የሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ “መካከለኛ ዘመን አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው” – የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች

3607

አዲስ አበባ ግንቦት 15/201 በፌደራልና አዲስ አበባ አስተዳደር የሚገኙ ተቋማት የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መካከለኛ ዘመን “በጤና እና ትምህርት ዘርፎች ዝቅተኛ አፈጻጸም ተመዝግቧል” ሲሉ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች ገለጹ።

የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመካከለኛ ዘመን አፈፃፀም ላይ ከወጣቶችና ከሴቶች አደረጃጀቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የተሳተፉ የአደረጃጀቶቹ አባላት በወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች በዕቅድ ዘመኑ የተሰሩት ስራዎች አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በጤናው ዘርፍ የተሰሩ በርካታ ስራዎች ቢኖሩም በቀጣይ ዓመታት ውስጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውንም አንስተዋል።

የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን መከላከልና መቀነስ፣ በእርግዝናና በወሊድ ወቅት ህይወታቸውን የሚያጡ እናቶችን ቁጥር መቀነስ፣ የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች፣ የመድሃኒት አቅርቦት ማነስ፣ የጤና ባለሙያዎች ስነ ምግባር ጉድለት በጤናው ዘርፍ ከሚታዩ ክፍተቶች መካከል እንደሚካተቱ አንስተዋል።

በትምህርት ዘርፍም የትምህርት ጥራት ጉድለቶች፣ በመንግስት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችና የግብዓት መጠን ያለመመጣጠን፣ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥና መድገም ችግሮች፣ የሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች መበራከትንም በጉድለት ገምግመዋል።

ወጣቶች፣ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያም የስራ እድል ፈጠራ በቂ ያለመሆን፣ የመስሪያ ቦታዎች ለገበያና ለስራ ምቹ ያለመሆን፣ የወጣት ማዕከላት እጥረት፣ የቤት ባለቤት ለማድረግ ያስቻለ መርሃ ግብር ያለመኖር ክፍተቶች ከተነሱት ውሰጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

የመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረቶችና የግንባታዎች ቅንጅት ጉድለት፣ ለከተማ ማደስና መልሶ ማልማት ስራዎች የተለዩ ቦታዎች ለዓመታት ታጥረው መቀመጣቸው፣ የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት አለመሟላትና ሌሎች ጉዳዮች ከሕብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚቀርቡና ያልተፈቱ አቤቱታዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ዓመታት “በዕቅድ ዘመኑ ውስጥ የተካተቱ ስራዎችን ለማሳካት ብዙ ስራዎች ይቀራሉ” ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ፎኢኖ ፎሌ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የቀረቡትን አስተያየቶችን “እንደ ግብዓት በመውሰድ ዕቅዱን ለመከለስና በቀጣይ ዓመታት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ርብርብ ይደረጋል” ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ ተደራሽነት ላይ ተጨባጭ ለውጦች መገኘታቸውን ጠቅሰው፤ ክፍተቶችና መታረም ያለባቸው ስራዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት ከፍተኛ በጀት ተመድቦ እየተሰራ ሲሆን፤ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ግን የማያቋርጥ ስራ የሚያስፈልገው መሆኑን ተናግረዋል።

የወጣቶችና የሴቶች ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይም “ጉድለቶችን በማስተካከል ተጠቃሚነታቸውን የሚጨምሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ብለዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በቅንጅት ለማከናወን በቅርቡ ወደ ስራ የገባው ተቋም በዘርፉ ያሉትን ችግሮች እንደሚፈታ እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመካከለኛ ዘመን አፈፃፀም ላይ እየተካሄደ ያለው ውይይት እስከ ግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ከአርሶና አርብቶ አደሮች፣ የግሉ ዘርፍና የሲቪል ማሕበረሰብ አካላት ጋር  በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።