ኮሚሽኑ ለወጣቶች ማዕከላት አራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

73
ድሬዳዋ ህዳር 7/2011 የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ለወጣቶች ማዕከላት ከአራት ሚሊዮን ብር  በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡ ድጋፉ የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያግዛቸው ወጣቶች ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ለማዕከላቱ  የለገሳቸው ከፌዴራል መንግሥት ባገኘውና በራሱ በጀት የገዛቸውን የማጣቀሻ መጻህፍት፤ ቴሌቪዥኞች፣ ለካፍቴሪያ የሚያገለግሉ ወንበሮችና የኤሌክትሮኒክስ ቁሶች ናቸው፡፡ በኮሚሽኑ ወጣቶችን የማሳተፍና የማብቃት አብይ የሥራ ሂደት መሪ አቶ ዋሲሁን አብርሃም ለኢዜአ እንደተናገሩት "የወጣት ማዕከላቱ የሚጠብቀውን ያህል አገልግሎት እየሰጡ ባይሆንም፤ የተደረገው ድጋፍ ችግሩን ያቃልለዋል" ብለዋል፡፡ ድጋፉ ለስምንቱ የከተማው ቀበሌዎችና ለአሰልሶ ገጠር ማዕከላት መከፋፈሉን የጠቆሙት የሥራ ሂደት መሪው፣ በሚቀጥሉት ሳምንታት ለመልካ ጀብዱ ቀበሌና ለሌሎች የገጠር ቀበሌዎች እንደሚሰራጭ ገልጸዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ወጣቶች ለተደረገው ድጋፍ አመስግነውድጋፍ በማዕከላቱ ካለው ክፍተት አንፃር በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሳቢያን ወጣቶች ማዕከል ቤተ-መጽሐፍት ውስጥ ሲገለገል የነበረው የ10ኛ ክፍል ተማሪው አሸናፊ ተካ ለማዕከሉ የተደረገው የመጻህፍት ድጋፍ  ለብሔራዊ ፈተና ለመዘጋጀት እንደሚያግዘው ተናግሯል፡፡ "በየማዕከሉ የዲ ኤስ ቲቪ አገልግሎት ቢሟላ የወጣቱን ችግር ይፈታል" ሲልም የወጣት እግር ኳስ ተመልካቾች ፍላጎት እንዲሟላ ጠይቋል፡፡ ወጣት ያሲን ዑመር በበኩሉ የወጣቱ ጥያቄዎች የፑልና የዲ ኤስ ቲቪ  አገልግሎቶች እንዲሟሉለት ቢጠይቅም፤ምላሽ አለመገኘቱን ይገልጻል። በቀበሌ 07 ወጣቶች ማዕከል የሚያገለግሉት አቶ መገርሣ መሐመድ የወጣቶች ማዕከላቱ የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጡ በባለሙያ፣ በአደረጃጀትና፣ በአሰራር በቁሳቁስ ያለባቸው መሠረታዊ ክፍተቶች በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ በኮሚሽኑ ወጣቶች የማሳተፍና የማብቃት ዓቢይ የሥራ ሂደት መሪ አቶ ዋሲሁን አብርሃም የወጣቶቹ ጥያቄዎች ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ይሟላሉ ብለዋል። ከከተማና ከገጠር ወጣቶች ጋር መድረክ በማዘጋጅት በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥር ነቀል መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም