የሙስናና የኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ሚናችንን እንወጣለን-የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች

63
ፍቼ ህዳር 7/2011 መንግሥት በሙስናና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ለማቅረብ በሚደረገው  ጥረት ሚናቸውን እንደሚወጡ የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች  ገለጹ፡፡ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎቹ እንደገለጹት መንግሥት ሙስናና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን  ለሕግ ለማቅረብ እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች ከመሆኑም በላይ፤መጪውን ጊዜ በተስፋ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡ የአገር ሽማግሌው ኮሎኔል  ገዝሙ ገቢሳ  የአገርንና የህዝብን ሀብት የመዘበሩ ብቻ ሳይሆኑ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በዜጎች ላይ የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ለማቅረብ የተጀመረው ጥረት እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። በቅኝ ግዛት  የተያዘ አገር  ላይ እንኳ  የማይፈፀም  ዘግናኝ  ዘረፋ  የመንግሥትን ሥልጣን መከታ በማድረግ ወንጀል  የፈጸሙ  ተጠርጣሪዎችን በሕግ እንዲዳኙ  መደረጉ የመንግሥትን አርቆ አስተዋይነት ስለሚያመለክት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አመልክተዋል ። ሕዝቡ ካለበት ድህነት ለመውጣት ሰላሙን  ከመጠበቅ ባሻገር ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ  መሰራት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡ የፍቼ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ  የሥነ-ልቡና ትምህርት መምህር  ጥላሁን በዳዳ  በበኩላቸው ''ታሪክ እንደሚያስረዳው  ጠንካራ ማህበረሰብና ትውልድ  የሚፈጠረው ቀደም ብሎ በተዘረጋው አመራር በመሆኑ  አሁን በአገሪቱ የሚከናወኑ የለውጥና የፍትህ ሥራዎች ትወልድን  በመቅረጽ  ፍሬያማ  ይሆናሉ” የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ወጣቱ  ራሱን ከስሜታዊነትና ከጀምላ  ፍረጃ በማራቅ ለሌሎች ከበሬታና ፍቅርን በማሳየት በጸረ ሙስና ትግሉ ምሳሌ ሊሆን እንደሚገባውም   አሳስበዋል ። ወንጀለኞችንና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን ለመታገል በመንግሥት የተጀመረውን  እንቅስቃሴ ልንደግፈው ይገባናል ብለዋል። መንግሥት  ወንጀልና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን ፈጽመዋል ያላቸውን ተጠርጣሪዎች ተከታትሎ ለፍርድ የማቅረብ  ሂደቱ አስደስቶኛል" ያለችው የፍቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ጥሩ ወርቅ አስፋው ናት፡፡ መርከብና አውሮፕላን  ለአገር ልማትና ጥቅም ከማዋል ይልቅ፤ ለግለሰቦች ጥቅም መዋላቸው እንዳሳዘናት ተናግራለች። ለወደፊቱም ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት የዝምድናና ወገናዊ አሰራር የሚቀርበት ዘዴ መቀየስ እንዳለበት ጠቁማለች፡፡ የሕዝብ ሀብት ያለ አግባብ ያባከኑ ተጠርጣሪዎች  በሕግ አግባብ መቀጣት አለባቸው ያለው ደግሞ  የዞኑ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር  አበራ ጋዲሳ ነው፡፡ የለውጥ እንቅስቃሴውን ከግብ ለማድረስ የሚያጋጥሙ  የሐሰት ወሬዎችን ከመመከት ጎን ለጎን ለውጡን ለሕዝብ ተደራሽ  ለማድረግ እንደሚሰራም አስታውቋል። ወጣቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ  ያለው ድርሻ  ከፍተኛ መሆኑን የተናገረው ሊቀመንበሩ፣ ፍትህን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሚናዬን እወጣለሁ ብሏል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም