የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎች ባለመቅረባቸው ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም—በፎገራ ወረዳ ሩዝ አምራች አርሶ አደሮች

1885

ባህር ዳር ህዳር 7/2011 የሩዝ ምርታማነትን የሚያሳድጉ የተሻሻሉ ዝርያዎች አለመቅረባቸውና የገባያ ትስስር አለመፈጠሩ ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርጎናል ሲሉ በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ ሩዝ አምራች አርሶ አደሮች ገለጹ።

በ200 ሚሊዮን ብር የተገነባው የፎገራ ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ስልጠና ማዕከል በወረታ ከተማ ተመርቋል።

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የሚገኙ ሩዝ አምራች አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት የሩዝ ምርታማነትን የሚያሳድጉ የተሻሻሉ ዝርያዎች ባለመቅረባቸውና እያመረቱ ለሚገኘው የሩዝ ምርት የገባያ ትስስር ባለመፈጠሩ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡

በወረዳው ሩዝ ከሚያመርቱ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ የሆኑት አርሶ አደር ማሩ ይመር ሩዝ አምርተው በሚያገኙት ገቢ ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያስተዳድሩ ተናግረዋል።

ላለፉት 20 ዓመታት “ኤክስ ጀግና” የተሰኘ የሩዝ ዝርያ ሲጠቀሙ እንደነበረና ይህም መሬቱን ከመለማመዱ የተነሳ የሚሰጠው ምርት እየቀነሰና በተደጋጋሚ በበሽታ እየተጠቃ በገበያ ላይም ተፈላጊነት እያጣ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

ቀደም ሲል ከአንድ ሄክታር እስከ 40 ኩንታል ምርት ያገኙ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ በአሁኑ ወቅት ምርቱ በሄክታር ወደ አምስት ኩንታል ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

የሩዝ ዝርያው በበሽታ የመጠቃት እድሉ እየሰፋ በመምጣቱ በሽታን የሚቋቋም የተሻለ የዘር አይነት እንዲቀርብላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም መፍትሄ ሊያገኙ እንዳልቻሉ አስታውቀዋል።

እንደ አርሶ አደር ማሩ ገለጻ ለሚያገኙት የሩዝ ምርትም የገበያ ትስስር ሊመቻችላቸው ባለመቻሉ ከቤት ፍጆታ ያለፈ ሸጠው ተጠቃሚ ለመሆን እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።

“ሸጋ” እና “ዋንዛየ” የተሰኙ የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎች ለአካባቢው ተስማሚ ከመሆናቸው ባለፈ በበሽታ የመጠቃት እድላቸው አነስተኛ በመሆኑ መንግስት እንዲያቀርብላቸው ቢጠይቁም መፍትሄ እንዳላገኙ የገለጹት ድግሞ አርሶ አደር የኋላ አስናቀው ናቸው፡፡

የሚያመርቱት የሩዝ ምርት አነስተኛ ቢሆንም የገበያ ትስስር ባለመመቻቸቱ ከዕለት ፍጆታ የተረፋቸውን ምርት ሽጠው ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ አብራርተዋል።

የወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማረ ገነቱ በበኩላቸው አርሶ አደሮች የሚያነሱት ችግር ትክክል መሆኑን አምነው “ለመፍትሄው ከፌዴራልና ከክልሉ የምርምር ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው” ብለዋል።

የገበያ ትስስርን ለመፈጠርም ተወካይ አርሶ አደሮችን ከዩኒየኖችና ነጋዴዎች ጋር የማገናኘት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።

ወረዳው ካለው የሰብል እርሻ መሬት ከ22 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለሩዝ ምርት ምቹ መሆኑን ያስረዱት አቶ አማረ አርሶ አደሮች በሚያነሷቸው ምክንያቶች የሚገባቸውን ጥቅም ሳይገኙ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

የፎገራ ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ስልጠና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሸዋዬ አበራ በበኩላቸው መንግስት በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ አገሪቱ ለሩዝ ምርት የሚመች የስነ-ምህዳር ባለቤት ብትሆንም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግር ምክንያት ዛሬም ከውጪ ለምታስገባው ሩዝ በዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ታደርጋለች።

“መንግስት ይህንን ከማስቀረት ባለፈ ሩዝ ወደውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት የመጀመሪያ የሆነውን ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ስልጠና ማዕከል በወረታ ከተማ ገንብቶ አስመርቋል” ብለዋል።

የምርምርና ስልጠና ማዕከሉ ዓላማ የተለያዩ የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎችን ማፍለቅና የሩዝ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን በማመቻቸት አርሶ አደሩን ለማገዝ መሆኑን አብራርተዋል።

አርሶ አደሮች የሚያነሱትን የገበያ ትስስርን ለመፍታት በአሁኑ ወቅት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በምርምርና ስልጠና ማዕከሉ የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው በዘርፉ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ከዘርፉ የሚጠበቀውን ገቢ ለማሳደግ የክልሉ መንግስት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ገዱ እንዳሉት በክልሉ ያለውን እምቅ የሩዝ ሀብት አሟጦ ለመጠቀምና የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሩዝ ምርት ለመልማት የሚችል መሬት መኖሩን ከፌዴራል ግብርና ምርምር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።