በምዕራብ ሸዋ ዞን ለሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ዝግጅት እየተደረገ ነው

1874

አምቦ ህዳር 7/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን በበጋው ወራት በ156 ሺህ 456 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ፈዬራ ኦሉማ ለኢዜአ እንደገለጹት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራው በተለዩ 529 ተፋሰሶች ላይ ይከናውናል።  

ከመጪው ጥር ወር መግቢያ በሚጀመረው የልማት ሥራ ከተለዩት ተፋሰሶች መካከል ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆነው መሬት ላይ የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን ሥራ ይከናወናል።

“ቀሪው የተራቆተ መሬትም ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተከልሎ እንዲጠበቅ ይደረጋል” ብለዋል አቶ ፈዬራ።

በልማት ሥራው 545 ሺህ 949 አርሶ አደሮችን ለማሳተፍ የሚያስችል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ኮንፈረንስ በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለሥራው የሚያስፈልጉ ዶማ፣ አካፋና ሌሎች አነስተኛ የነፍስ ወከፍ የልማት መሳሪያዎችም ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች በበኩላቸው እንዳሉት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በመረዳታቸውም ዘንድሮ ለሚያከናውኑት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ከወዲሁ እየተዘጋጁ ናቸው።

የአምቦ ወራዳ አርሶ አደር ንጋቱ ተፈራ ባለፉት ሰባት ዓመታት በአካባቢያቸው በተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች የማሳቸው የአፈር ለምነት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የመሬት ለምነት በመሻሻሉም ቀደም ሲል ከአንድ ሄክታር ማሳቸው ያገኙት የነበረው 25 ኩንታል የበቆሎ ምርት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእጥፍ እንዳሳደገው ገልፀዋል፡፡

የተፋሰስ ሥራ ምርታማነታቸውን በማሳደጉ ዘንድሮ ለሚከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ያለማንም ቀስቃሽ ለመሳተፍ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ በዞኑ የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አርሶአደር መረራ ፋና ናቸው፡፡

አርሶ አደሩ እንደሚሉት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ሥራ በተለይ ለግብርና ሥራቸው ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገላቸው ነው።

” በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ያወደምነው የተፈጥሮ ሃብት የመሬት ለምነትን በመቀነሱ ማሳዬ ሰብል ማብቀል ወደማቆም ደረጃ ተቃርቦ ነበር” ያሉት ደግሞ የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ሰኚ መንግስቱ ናቸው።

ከ2004 ጀምሮ በአካባቢያቸው ሲከናወን በቆየው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የመሬታቸው ለምነት ወደነበረበት መመለሱን ተናግረዋል።

” የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በተጨባጭ በመረዳቴም ዘንድሮ ለሚሰራው ሥራ ከወዲሁ ተዘጋጅቺያለሁ ” ብለዋል አርሶ አደር ሰኚ።

በምዕራብ ሸዋ ዞን ለተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ባለፉት ሰባት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ከ9 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት ማገገሙ ታውቋል።