በነቀምቴ ከተማ 10 ሕጻናት በጉዲፈቻ ተሰጡ

84
ነቀምቴ ህዳር 7/2011 በምሥራቅ ወለጋ ዞን በነቀምቴ ከተማ 10 ሕጻናት በጉዲፈቻ መሰጠታቸውን የከተማው ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ገለጸ። ሕጻናቱ ለአሳዳጊዎች የተላለፉት ዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀን ትናንት በከተማው በደማቅ ሁኔታ በተከበረበት ወቅት ነው። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ታደሰ በዚሁ ወቅት አገር ተረካቢ ትውልድ የሆኑትን ወላጅ አልባ ሕጻናትን መንከባከብና መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል። የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ጫላ ገመዳ በበኩላቸው ሕፃናትን መንከባከብ የወላጅና የዘመድ ብቻ ሳይሆን፣ የኅብረተሰቡ ድርሻ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት አመልክተዋል። ሕፃናት የተለየ ትኩረትና እንክብካቤ እንደሚሹ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ጉዲፈቻ ከወሰዱት እናቶቸ መካከል የ03 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ፈቃዱ በሰጡት አስተያየት የተረከቡት ሕፃን እንደወለዱት ልጅ ጽዳቱን፣ምግቡንና የሚያስፈልገውን ሁሉ በማሟላት ለማሳደግ ቃል ገብተዋል። የሶርጋ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ቡሼ በንቲ በበኩላቸው የተረከቡትን ልጅ  ከአንድ ልጃቸው ለይተው እንደማያዩትት ገልጸዋል። በበዓሉ ላይ የሕፃናት መዝሙር፣ግጥሞችና ጣዕመ ዘማዎች ቀርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም