የትግራይ ክልል ምክር ቤት ባካሔደው አስቸኳይ ጉባኤ አዳዲስ ሹመቶችንና አዋጆችን አጸደቀ

71
መቀሌ ግንቦት 15/2010  የትግራይ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ያካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ሁለት አዋጆችንና ሁለት የቢሮ ኃላፊዎችን ሹመት በማጽደቅ ተጠናቋል። ምክር ቤቱ ህወሐት ያካሄደውን ጥልቅ ተሐድሶ ተከትሎ በክልሉ ቀደም ሲል በስፋት ይታይ የነበረውን የተዛባ የሃሰት ሪፖት ለማስቀረት እንዲቻል  የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጅን አጽድቋል። እንዲሁም በክልሉና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚነደፉ ፖሊሲዎችንና የሚሰጡ ውሳኔዎችን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ የክልሉን የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ በሙሉ  ድምጽ አጽድቆታል። በተጨማሪም የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒምና የምስራቃዊ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት ወይዘሮ የዓለም ጸጋይ ለሌላ ኃላፊነት ወደ ፌዴራል በመሔዳቸው አዳዲስ ተሿሚዎችን መድቧል። በዚህ መሰረትም ወይዘሮ ሰብለ ካህሳይን በሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊነት እንዲሁም አቶ ሺሻይ መረሳን ደግሞ በምስራቃዊ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪነት በመሾም ጉባኤው ተጠናቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም