ደብረ ብርሃን አዲስ ማስተር ፕላን ሊሰራላት ነው

118
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 የደብረ ብርሃን ከተማ አዲስ ማስተር ፕላን ልትተገብር መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ። በአስተዳደሩ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስከያጅ አቶ ሰለሞን ጌታቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የደብረ ብርሃን የከተሜነት ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ ዕድገት አሳይቷል። በዚህም ለ10 ዓመት በሚል ከአራት ዓመት በፊት የተሰራው የከተማ ማስተር ፕላን የዕቅዱን ግማሽ ዓመታት ሳይደፍን ተጠናቋል። በዚህም ሶስት ሺህ ሄክታር መሬት ማስፋፊያ የተጨመረበት አዲስ ፕላን መሰራቱን ተናግረዋል። ከዚህም ውስጥ ሁለት ሺህ ሄክታሩ ለኢንዱስትሪ ሲሆን ቀሪው አንድ ሺህ ሄክታር ደግሞ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል ነው ተብሏል። በማስተር ፕላኑ የተካተቱ የማስፋፊያ ስራዎች እንደተጠናቀቁ በሚመለከተው አካል ማረጋገጫ ተሰጥቶ በቅርብ ወራት ወደትግበራ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም