ፍርድ ቤቱ አቶ ያሬድ ዘሪሁን የህግ ባለሙያ አማክረው ለህዳር 11 እንዲቀርቡ የጠየቁትን ጥያቄ ተቀበለ

81
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ያሬድ ዘሪሁን የህግ ባለሙያ አማክረው እንዲቀርቡ የጠየቁትን ጥያቄ ተቀበለ። በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የተያዙት አቶ ያሬድ ዘሪሁን ባለሙያ አማክረው ለመጪው ማክሰኞ 2011 ዓ.ም እንዲቀርቡ ተፈቅዷል። ዛሬ ከሰዓት በኋላ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት የቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት  ምክትል ኃላፊ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ያሬድ ዘሪሁን አቶ ጌታቸው አሰፋ ከተባሉ የስራ ባልደረባቸው ጋር በማበርና በጥቅም በመተሳሰር የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን ፖሊስ ገልጿል። ተጠርጣሪው ሰዎችን ያለአግባብ ለእስር በመዳረግ፣ በህግ ባልተፈቀዱ ቦታዎች በማሰር እንዲሁም በማንገላታትና ራቁታቸውን በማሰር ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። በዛሬው ችሎት ተጨማሪ ማስረጃ ለማቅረብ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል። ተጠርጣሪው በበኩላቸው ለማክሰኞ ህዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም የህግ ባለሙያ አማክረው ለመቅረብ ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱም በዚሁ መሰረት የህግ ባለሙያ አማክረው እንዲቀርቡ ፈቅዷል። በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩት አቶ ያሬድ በቁጥጥር ስር የዋሉት በዱከም ከተማ በፌዴራል ፖሊስና በኦሮሚያ ፖሊስ ክትትል መሆኑ ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም