በጋምቤላ ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ተደርጎ ይሰራል...አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

59
ጋምቤላ ህዳር 7/2011 የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በህዝብ ለተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጡ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ አስታወቀ። አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ ሊተገበሩ የታቀዱ የልማት ሥራዎችን አስመልክተው  መግለጫ ሰጥተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በመግጫቸው እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍች የሚያበረታቱ የልማት ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም ህዝቡ በሚፈልገው ልክ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል። በእዚህም የህዝቡ የልማት ጥያቄዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውንና የሰላምና የመልካም አስተዳዳር ችግር እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል። አቶ ኡሞድ እንዳሉት በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት በማስፋን በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የመፍታቱ ተግባር የክልሉ መንግስት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል። የክልሉን ህዝብ ኑሮ ይለውጣል ተብሎ የተካሄደውን የመንድር ማሰባሰብ መረሃግብር በማጠናከርና ተጀምረው ፍጻሚያቸውን ያላገኙ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ የማድረጉ ሥራም ትኩረት እንደሚሰጠው አመልክተዋል።     በክልሉ የተሻለ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት በመዘርጋት በየዓመቱ የሚያጋጥመውን የደመወዝ ክፍያና የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ በጀት እጥረት ችግር ለመፈታት የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደረግም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። የክልሉን ልማት እየተፈታተነ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሙስናና ብልሹ አሰራር ችግሮችን የማስወገዱ ተግባር ሌለው ልዩ ትኩረት ተስጥቶበት የሚሰራበት ጉዳይ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልከተዋል። " በኢንቨስትመንት ስም በገጠርና በከተማ ተይዘው ወደ ልማት ያልገቡ መሬቶች የህዝብና የመንግስት ሀብቶች በመሆናቸው ወደ መሬት ቋት ለማስመለስም በቅንጅት ይሰራል " ብለዋል አቶ ኡሞድ።  እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ የህግ የበላይነትን በማስጠበቅ ዜጎች ሰብአዊና ዴሞከራሰዊ መብታቸው እንዲከበርና ከብልሹ አሰራር የጸዳ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ የክልሉ መንግስት በትኩረት ከሚሰራበቸው ዘርፎች መካከል ይጠቀሳል። "በክልሉ በተለይም ከተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ በወጣቶችና በሴቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታትም የክልሉ መንግስት በአጽኖት ይሰራል" ብለዋል። በክልሉ ሊተገበሩ የታቀዱ የልማት እቅዶችን ወደውጤት በመቀየር በኩል አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበው ህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎውን እንዲያጠናክርም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም