የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋኑ 57 በመቶ ደርሷል-የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል

127
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010  በገጠርና ከተማ ያለውን የኤሌትሪክ ኃይል ሽፋን 57 በመቶ ማድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሰራተኞች እና አመራሮች በዛሬው እለት 27ኛውን የግንቦት 20 ድል በዓል "የላቀ ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ  አንድነት ለላቀ አገራዊ ስኬት" በሚል መሪ ሐሳብ በውይይት አክብረዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጪ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ እንዳሉት፤ ባለፉት 27 ዓመታት አገሪቷ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አቅሟን በስፋት እያሳደገች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት በገጠርና በከተማ ያለው የኤሌትሪክ ሽፋን 57 በመቶ እንደደረሰ ጠቁመው፤ በዚህም 6 ሺ 387 የከተማና የገጠር ማዕከላት ኤሌክትሪክ ማግኘታቸውን ተናግዋል። ከ27 ዓመታት በፊት የስርጭት ሽፋኑ ስምንት በመቶ እንዲሁም 320 ከተማዎች ብቻ የተወሰነ እንደነበር አስታውሰዋል። ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት የኤሌክትሪክ ኃይል ከ370 ሜጋ ዋት ወደ 4 ሺ 260 ሜጋ ዋት መድረሱንም ጠቅሰዋል። "በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለማቃለል ስትራቴጂክ እቅድ ተነድፎ እየተሰራ” መሆኑንም ነው  አቶ ምስክር የገለጹት፡፡ ከውኃ 50 ሺ ሜጋ ዋት፣ ከነፋስ 1 ነጥብ 3 ሚሊዬን ሜጋ ዋት፤ ከምድር እንፋሎት ከ10 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል እድል መኖሩን ተናግረዋል። ስለዚህም በቀጣይ የአገሪቷ ሁሉም አካባቢዎች ደረጃ በደረጃ የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ምስክር ጠቅሰዋል። ጭስ አባይ ሁለተኛ  72 ሜጋ ዋት፣  ጊቤ አንድ 184 ሜጋ ዋት፣ ተከዜ ሶስት 300 ሜጋ ዋት፣ ጊቤ  ሁለት 420 ሜጋ ዋት፣ ጣና በለስ 460 ዋት፣ ጊቤ ሶስት 1870 ሜጋ ዋት ኤልክትሪክ ኃይል ያመነጫሉ። ከአዳማ አንድና ሁለት እንዲሁም ከአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች ደግሞ 324 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተችሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም