እርምጃው መንግሥት ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለሕግ የበላይነት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ የደቡብ ክልል መንግሥት አስታወቀ

60
ሃዋሳ ህዳር 6/2011 መንግሥት ሰሞኑን እየወሰደ ያለው እርምጃ ለሰብዓዊ መብት መከበር፣ ለፍትህና ለሕግ የበላይነት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ የደቡብ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ  መንግሥት አስታወቀ። የክልሉ መንግሥት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  በላከው መግለጫ እንደገለጸው የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ለዜጎች አለኝታነት መቆም ነው፡፡ በአገሪቱ በህዝብ ግፊት የተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ ውጤታማ እንዲሆን እየተወሰደ ያለውን እርምጃ መንግሥት በሰከነና ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ መረጃዎችን በማሰባሰብና በማስረጃ በማስደገፍ ማከናወኑን አመልክቷል። ይህም በአገሪቱ የተፈጸመውን ሕገ ወጥ ተግባር ለማጋለጥና ለማስቆም የተሄደበትን በመሆኑን  አድናቆቱን ገልጿል፡፡ ሕገ ወጥነትን ለማስፋፋት ራሳቸውን ከሕግ በላይ በማድረግ በአገርና በዝብ ሃብት ላይ ከፍተኛ በደል ሲፈጽሙ የቆዩ አካላት አገርን የማፍረስ እኩይ ተግባራቸው በማስረጃ በማስደገፍ መቅረቡ ተገቢ ነው ብሏል፡፡ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚጎዱ ተግባራት ሲፈጽሙ፣ የዜጎችንና የቡድኖችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብት የጣሱ እንዲሁም መንግሥታዊ ልጣንን ለሽብር ተግባር ማስፈጸሚያ ሲውል እንደነበርም ማሳየቱንም አመልክቷል፡፡ መንግሥት ሕዝብን የሚጠቅም ለውጥ ማምጣት እንደሚገባው በማመን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን የጠቀሰው መግለጫው፣ የሰሞኑ እርምጃውም የዚህ አካል ነው ብሏል፡፡ በሰው ልጆች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችንና በአገሪቱ ላይ ከባድ ሙስና ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር በማዋል የሕግ የበላይነት እንዲከበር የተያዘው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግሥት ጠይቋል፡፡ እርምጃውም ማንኛውም ሰው ወንጀል ሰርቶ በሕግ ከመጠየቅ ማምለጥ እንደማይችልና ማንም ከሕግ በላይ እንዳልሆነ ያሳያል ሲልም አመልክቷል፡፡ የአስተዳደር ብልሹነትና ሌብነትን ለማስቀረት የሚደረገው ትግል የመንግሥትና የሕዝብን ጠንካራ ቁርኝት እንደሚሻ ያስረዳው መግለጫ፣የክልሉ መንግሥት የሕግ የበላይነት እንዲከበር የሚወሰደው እርምጃ እንዲጎለብት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጧል፡፡ የክልሉ ሕዝብም ከመንግሥት ጎን በመቆም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም