የድርጅቶቹ ስምምነት በምዕራብ ኦሮሚያ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር እንደሚያቃልል የገምቢ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

55
ጊምቦ ህዳር 6/2011 የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)ና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በጋራ ለመስራት ያደረጉት ስምምነት በምዕራብ ኦሮሚያ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር ለማቃለል እንደሚያስችል የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት ድርጅቶቹ  የተፈራረሙት ስምምነት በምዕራቡ የክልሉ ክፍሎች የሚታየውን  የፀጥታ ችግር ለመፍታት ሚና ይኖረዋል። አቶ አበራ በቀለ የተባሉት ነዋሪ በሰጡት አስተያየት የድርጅቶቹ  አመራሮች ያደረጉት ስምምነት እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ለአገር ሰላምና ልማት እንዲሁም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በጋራ ለመሥራት መወሰናቸው ለአገሪቱ ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል። ወጣት ዜኒት ዓሊ በበኩሏ ፓርቲዎቹ የሚያገለግሉት አንድን ሕዝብ እስከሆነ ድረስ ልዩነቶታቸውን በማጥበብ  ሕይወቱን ለማሻሻል ራዕይ አንግበው መሥራት ይኖርባቸዋል ብላለች። በዚህም ድርጅቶቹ ለሰላምና ልማት አብረው ለመቆም መወሰናቸው እንዳስደሰታት ገልጻለች። ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ተመስጌን ዋቅጋሪ በሰጡት አስተያየት ስምምነቱ የፀጥታውን ሁኔታ እንደሚያሻሽልና ኅብረተሰቡም በሚጠበቀው ደረጃ ሳይለማ የቆየውን አካባቢውን ከስጋት ወጥቶ እንዲያለማ ያደርገዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። አቶ አበራ የማነ በበኩላቸው ድርጅቶቹ ለአገር እድገትና ሰላም ለመሥራት መወሰናቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ልዩነቶችን አጥብቦ ለአገር ግንባታ አንድ ላይ መቆምን ከነሱ መማር ይኖርባቸዋል ብለዋል። በኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳና በኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የተመሩት የልዑካን ቡደድኖች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸው ስምምነት የደረሱት ትናንት ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም