ፍጹም ገብረ ማሪያም በዓመቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ልዩ ተሸላሚ ሆኗል

77
አዲስ አበባ 6/2011 ፍጹም ገብረ ማሪያም የ2010 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ስፖርታዊ ጨዋነት ልዩ ተሸላሚ ሆነ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ዓመት ባካሄዳቸው ውድድሮች በተጫዋችነት፣ በአሰልጣኝነት፣ በግብ ጠባቂነትና ሌሎች ዘርፎች ኮከቦችን ሸልሟል። በዚህም መሰረት የመከላከያ እግር ኳስ ክለቡ ፍጹም ገብረ ማሪያም በዓመቱ ባሳየው ስፖርታዊ ጨዋነት ልዩ ተሸላሚ ሆኗል። ፍጹምን ለሽልማት ያበቃው አዲስ አበባ በተካሄደው 22ኛው ሳምንት የመከላከያና የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጨዋታ ላይ የተከሰተውን አለመግባባት ተከትሎ በዳኛው እያሱ ፈንቴ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ለመከላከልና ግጭቱን ለማብረድ ባደረገው ጥረት ነው። በውድድር ዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ የሆነው ደግሞ ጅማ አባጅፋር ፕሪሚየር ሊጉን በተቀላቀለበት በመጀመሪያው ዓመት ዋንጫ እንዲያነሳ ላበቃወ  አሰልጣኝ ገብረመድህን ኋይሌ ነው። በፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም መሐመድ ሲሆን ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ የተሸለመው ደግሞ   የጅማ አባጅፋሩ ዳንኤል አጃዬ ነው። ሌላው የጅማ አባጅፋር ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ በኮከብ ግብ አግቢነት ተሸላሚ ሆኗል፤ የክለቦች የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫንም ይኸው ክለብ  ወስዷል። በከፍተኛ ሊግ ውድድር በኮከብ ተጫዎችነት ብሩክ ኤሊያስ ከደቡብ ፖሊስ፤ ኮከብ ግብ ጠባቂ የባህዳር ከተማው ምንተስኖት አሎ ተሸላሚ ሆነዋል። በከፍተኛ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የተሸለመው የጅማ አባቡናው ብዙአየሁ እንዳሻው ነው። የደቡብ ፖሊሱ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በከፍተኛ ሊጉ በኮከብ አሰልጣኝነት ተመርጧል። በሴቶች የፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ጨዋታ የአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር የደደቢት ክለቦቹ  ሰናይት ቦጋለ በኮከብ ተጫዋችነት፣ ሎዛ አበራ በኮከብ ግብ አግቢነት እንደዚሁም  ገነት አክሊሉ በኮከብ ግብ ጠባቂነት ተሸላሚ ሆነዋል። በሴቶች የፕሪሚየር ሊግ ስፖርታዊ ጨዋነት አዳማ ከተማ ተሸላሚ ሆኗል። በሴቶች የፕሪሚሪሊግ እግር ኳስ አንደኛ ዲቪዚዮን ኮከብ አሰልጣኝ የደደቢት ክለቡ ኤልያስ ኢብራሂም ሆነዋል። በሌሎችም ፌደሬሽኑ በሚያዘጃቸው የአንደኛ ሊግ፣ ከ17 እና 20 ዓመት በታች  ውድድሮች ተካፍለው በተጫዋችነት በግብ ጠባቂነት፣ ከፍተኛ ጎል ላስቆጠሩና በዳኝነት የተሻለ አቋም ላሳዩ ሽልማት ተበርክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም