በአገሪቷ የስቶክ ማርኬት ለመጀመር የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ማሟላት አለባቸው - ምሁራን

148
አዲስ አበባ  ኅዳር 6/2011 በኢትዮጵያ ስቶክ ማርኬት (የድርሻ ሽያጭ ገበያ) ለመጀመር የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እንደሚገባ የምጣኔ ኃብት ምሁራን ገለጹ። መንግሥት በተያዘው ዓመት የነጻ ገበያ ሕግጋትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደርግ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  በምክር ቤቶች የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የመንግስታቸውን አቋም ሲገልጹ መናገራቸው ይታወሳል። ምሁራኑ አንደሚሉት ታዲያ የስቶክ ማርኬት በኢትዮጵያ መጀመር ቢኖርበትም የአገሪቷ ወቅታዊ የምጣኔ ኃብት ቁመና ሥርዓቱን ለመዘርጋት አቅሙ በቂ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። ይሁንና ሥርዓቱ ለአገሪቷ እድገት ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽዖ ስለሚኖረው መንግሥት ለገበያ ሥርዓቱ የሚያመቹ ቅድመ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለበት ጠቅሰዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ብርሃኑ እንደሚናገሩት ስቶክ ማርኬት የገንዘብ እጥረትን ለመፍታት ወሳኝ በመሆኑ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ በቅድሚያ የአገሪቷ ማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት እንዳለበትና በተለይም የውጭ ምንዛሬ ተመን መዋዠቅን ተቆጣጥሮ የወለድ ተመንን ማረጋጋት ያስፈልጋል ብለዋል። ጎን ለጎንም ለገበያ ሥርዓቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ (ሊኪዩዲቲ) የሚያቀርበው ባንክ ጠንካራና ከስቶክ ማርኬት ጋር የሚቀናጅበት ደረጃ ላይ መድረስ አለበት ነው ያሉት። የሰው ኃይሉም የሠለጠናና በዘርፉ ልምድ ያለው መሆን እንዳለበት ጠቁመው በተጓዳኝም ጠንካራና ገለልተኛ የፍትህ ሥርዓቱም መዘርጋትም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በሌላ በኩል በፋይናንስ ሥርዓት ላይ ያለው ቁጥጥርና ማጠናከር የሚቻል ከሆነ ስቶክ ማርኬት (የድርሻ ሽያጭ ገበያ) በአገሪቷ ፍሬያማ ሊሆን እንደሚችል ነው የተናገሩት። በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ አቶ ፋሲል ጣሰውም በተመሳሳይ ስቶክ ማርኬት ለመጀመር የሚያስችል የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ መኖሩን ማረጋጋጥ ያስፈልጋል ይላሉ። በፊሲካል ፖሊሲው በተለይም የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱን ማዘመንና ማጠናከር እንዲሁም የገንዘብ ፖሊሲዎቹ ነጻ ገበያን መሰረት ባደረገ መልኩ መቃኘት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። በተጓዳኝም ስቶክ ማርኬት የውጭ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማትን ሊጋብዝ የሚችል ሥርዓት በመሆኑ በውጭ ባንኮች አንዳይወጡ ጠንካራ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል። በተመሳሳይም የስቶክ ማርኬት የገበያ ሥርዓትን ለማሳለጥ የሚያሰችሉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማሟላትም ሊተኮርበት ይገባል ነው ያሉት። የፌር ፋክስ ግሎባል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው ስቶክ ማርኬት በኢትዮጵያ ለመጀመር ሙከራ ካደረጉት ግለሰቦች ወስጥ አንዱ መሆናቸውን ይናገራሉ። ያም ሆኖ አንዳንድ ምርቶች ኢትዮጵያ ተመርተው ውጭ አገር የሚሸጡበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው ይህም ይፋዊ ያልሆነ የስቶክ ማርኬት እንቅስቃሴ መኖሩን ያሳየል ብለዋል። አሁን ላይ ይህንን የገበያ ሥርዓት ሊያሳልጥ የሚያስችል ሕጋዊ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በአገር ውስጥ ስቶክ ማርኬት ደረጃም ቢሆን ገበያው መጀመር  አለበት የሚል ግምት አላቸው። በቅርቡ የዓለም ገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የመንፈቅ ዓመት ግምገማ መሰረት የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ግምገማ አዎንታዊ መሆኑን
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም