የምዕራብ ሸዋ ዞን የተለያዩ አካላት ለተፈናቃዮች 665 ሺህ ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ

333

አምቦ ህዳር 6/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኙ የተለያዩ አካላት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በምሥራቅ ወለጋ ዞን ለተጠለሉ ወገኖች 665 ሺህ ብር ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን ያደረጉት በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ምዕራብ ሸዋ ቅርንጫፍ፣ የአምቦ የገበሬዎች ኀብረት ሥራ ዩኒዬንና የዞኑ የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው ።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ቀይ መስቀል ማህበር ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ መኮንን ትናንት በነቀምቴ ከተማ ድጋፉን ለሚመለከታቸው የአስተዳደር አካላት አስረክበዋል ።

ከድጋፉ መካከል 355 ኩንታል እህል፣17 ኩንታል ስኳርና አልባሳት ይገኙበታል ።

በነቀምቴ መጠለያ ጣቢያ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል ወይዘሮ ጎዴ ቀናቴ ድጋፉ የተፈናቃዮችን ችግር እንደሚያቃልል በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

“የኦሮሚያና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥታት ተፈናቃዮች ወደ ቀያችን ተመልሰን በዘላቂነት ኑሯችንን እንድንቀጥል መፍትሄ ሊፈልጉ ይገባል” ብለዋል ።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገመቺስ ተመስጌን ተቋማቱና ሠራተኞቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ።