ኢቦላን ለመከላከል በሁለቱ ዓለም ዓቀፍ ኤርፖርቶች ምርመራ ተጀመረ

3591

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች የኢቦላ በሽታን ለመከላከል በተጓዦች ላይ ምርመራ መጀመሩን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢቦላ በሽታ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መከሰቱን ተከትሎ መንግስት የመከላከል ቅድመ ዝግጅት እያከናወነ ይገኛል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ግብረ-ኃይል በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ተቋቁሞ የተቀናጀ የመከላከል ስራ ጀምሯል ብለዋል።

በዚህም መሰረት የኢቦላ ወረርሽኝን አስቀድሞ ለመከላከል በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎችና በረራዎች የምርመራ ስራ መጀመሩን ነው የተናገሩት።

ኢቦላ በድጋሚ ከተከሰተባት ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና አካባቢው አገራት እንዲሁም በቅርቡ ወደ አገራቱ ተጉዘው በነበሩ የአየር መንገዱ ደንበኞች ላይ ምርመራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በየብስ ትራንስፖርት መግቢያና መውጫ ባላቸው 30 የአገሪቱ አዋሳኝ ድንበሮች የፍተሻ ቁጥጥር መጀመሩንም አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማና በክልሎች የኢቦላ ምልክት በሚታይበት ጊዜ የማቆያ ማዕከላት፣ መድሃኒትና የመከላከያ መሳሪያዎች ዝግጁ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኮንጎ ወገኖቻችንን ከመርዳትና ከመተባበር አኳያ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በቅርበት በመነጋገር ጉዳዩን እየተከታተልን እንገኛለን ብለዋል።

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሆና የሰው ኃይልም ሆነ ሌላ እርዳታ ለማድረግ ዝግጁ ናት ነው ያሉት ሚኒስትሩ።