የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሰላ እየተካሄደ ነው

742

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 ስድስተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በአሰላ አረንጓዴው ስታዲየም ተጀምሯል።

የውድድሩ ውጤታማ አትሌቶች በመጪው ሐምሌ 2010 ዓ.ም በፊንላንድ ቴምፔሬ ከተማ በሚካሄደው የዓለም ወጣቶች አትሌቲከስ ሻምፒዮና አገራቸውን ወክለው የሚካፈሉ ይሆናል።

ከዚህ በተጨማሪ ውድድሩ መደረጉ ቀጣይ ለአገሪቱ አትሌቲክስ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ይጠቅማል ተብሏል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ውድድር በመክፈቻው አምስት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።

ከፍጻሜ ውድድሮች መካከል የ10 ሺህ ሜትር የወንዶች ፍጻሜን አትሌት በሪሁ አረጋዊ ከሱር ኮንስትራክሽን በአንደኝነት አጠናቋል።

አትሌት ኦሊቃ አዱኛ ከኦሮሚያ ክልል እንዲሁም ጸጋዬ ኪዳኑ ከመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ሌሎች ፍጻሜቸውን ካገኙ ስፖርቶች መካከል የዲስከስ ውርወራ በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በወንዶች የስሉስ እና ርዝመት ዝላይ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ዛሬ የአምስት ሺህ ሴቶችን ጨምሮ ሌሎች ስድስት ውድድሮች ላይ ማጣሪያ ተካሂዷል።

የሴቶች የአምስት ሺህ ሜትር፣ በ800 ሜትር ሴትና ወንድ እንዲሁም በወንዶች የመዶሻ ውርወራና ምርኩዝ ዝላይ ነገ የሚካሄዱ የፍጻሜ ውድድሮች ናቸው።

በኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ከጋምቤላ ክልል ውጭ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም 34 የተለያዩ  ክለቦችና ተቋማት ተካፋይ ሆነዋል።

ለውድድሩ ፌዴሬሽኑ ድጋፍ የሚያደርግ ቢሆንም የጋምቤላ ክልል ግን መካፈል አልቻለም።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ ለኢዜአ ጋምቤላ እንደሌሎች ክልሎች እንዲሳተፍ አሳውቀናል፤ ለምን እንዳልተሳተፈ ግን የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል።

በዚህ ውድድር የሚካፈሉት እድሜቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ ስፖርተኞች ሲሆኑ በቀጣይ አገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶችን ለማግኘትም ነው።

ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ተወዳዳሪዎች  በተባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ናቸው ለማለት አያስደፍርም።

የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም የዕድሜ ተገቢነት ችግር አሁንም ሊፈታ ያልቻለ ጉዳይ ነው ብሏል።

ፌዴሬሽኑም ይህን መቆጠጣር አስቸጋሪ እንደሆነበትና ክልሎችና ክለቦች ሲጠየቁ ክለብ ሲገባ ዕድሜውን እንዲቀንስ ተደርጎ የተመዘገበበትን ሀሰተኛ የሆነ ማስረጃ ያቀርባሉ ነው ያለው።

በዚህ ምክንያት ዕድሜቸውን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑን ነው የተናገረው።

በዚህ ምክንያት በትክክለኛው የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ታዳጊዎች ማግኘት ያለባቸውን ዕድል የሚነፍግ በመሆኑ ክልሎችና ክለቦች በተገቢው የዕድሜ ክልል ያሉ ስፖርተኞችን በመላክ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስቧል።