በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 72 ሺህ 900 የአሜሪካን ዶላር ተያዘ

121
አዳማ ህዳር 6/2011 በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 72 ሺህ 900 የአሜሪካን ዶላር መያዙን ፖሊስ አስታወቀ። ዶላሩን ይዞ የነበረ ተጠርጣሪም በቁጥጥር ስር ውሏል ። የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዋና ሳጂን ወርቅነሽ ገልሜቻ  ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ዶላሩ የተያዘው ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ በመጓዝ ላይ በነበረ ኮድ 3-03952 ድሬ ፒክ አፕ ተሽከርካሪ ውስጥ ነው። "ፖሊስ ከህብተሰሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ተሽከርካሪው ትላንት ከምሽቱ ሁለት ሰአት ተኩል ላይ በአዳማ ከተማ ዳቤ ሶሎቄ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኬላ አካባቢ ሲደርስ ባደረገው ፍተሻ ዶላሩ በአንድ መንገደኛ ሻንጣ ውስጥ ተደብቆ ተገኝቷል" ብለዋል። ዶላሩን ይዞ የተገኘው ተጠርጣሪም በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል። በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ ተባብሯል የተባለ አሽከርካሪ ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ሳጅን ወርቅነሽ  ገልፀዋል። እንደ ሳጅን ወርቅነሽ ገለጻ ተሽከርካሪው10 ሰው አሳፍሮ በመጓዝ ላይ ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም