ሰራዊቱ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት አዲስ የሰላም ማስከበር አሰራር ለዓለም አስተዋውቋል

1723

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተሰማራቸባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከሚሰጠው ግዳጅ ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት አዲስ የሰላም ማስከበር አሰራር ለዓለም ማስተዋወቅ መቻሉ ተገለጸ።

ሰራዊቱ በህዝባዊ ወገንተኝነት ምግባሩ ባለፉት ሁለት አስርት-ዓመታት ኢትዮጵያ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተመራጭ አገር ሆና እንድትቀጥል አድርጓል ነው የተባለው።

ኢዜአ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ የኢትዮጵያ ተመራጭነት እየጨመረ መምጣቱን አስመልክቶ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን አነጋግሯል፡፡

ወታደራዊ ኃላፊዎች እንደሚሉት፤ ባለፉት ሁለት አስርት-ዓመታት በኢትዮጵያ ሰራዊት ዘንድ የተፈጠረው ህዝባዊ አስተሳሰብን በሰላም ማስከበር ተልዕኮ መተግበር በመቻሉ አገሪቱን ለተልዕኮው ተመራጭ አድርጓታል።

በኢትዮጵያ የዓለማቀፍ የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ኃብታሙ ጥላሁን “የኢትዮጵያ ሰራዊት ሰላም የሚያስከብረው በምሽግ ታጥሮ ሳይሆን ከህዝብ ጋር በመቀላቀል፤ ከህዝብ ጋር እየኖረ ነው” ይላሉ።

ይህም ኢትዮጵያ በዓለምአቀፍ ወታደራዊ ተልዕኮ እንድትሳተፍ ያለማቋረጥ ጥያቄ እንዲቀርብላት አድርጓል ነው ያሉት።

ሰራዊታችን ግዳጁን በብቃት ከመፈጸም ጎን ለጎን በሚሄድባቸው አካባቢዎች ሁሉ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት መቻሉ ተፈላጊ እንዳደረገው የተናገሩት ደግሞ በማሰልጠኛው የወታደራዊ ታዛቢዎችና የስታፍ መኮንኖች የስልጠና ክፍል ኃላፊ ኮሎኔል ታምራት አንዳርጌ ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ለስምሪት አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ሳይቀር ግዳጁን በብቃት እንደሚወጣ አስታውሰው፤ ለሶማሊያ ሰላም የከፈለውን መስዋዕትነት ለአብነት አንስተዋል።

ሰራዊቱ በሄደባቸው አካባቢዎች በሚያሳየው ህዝባዊነት አዲስ የሰላም ማሰከበር አሰራርን ለዓለም ማስተዋወቁንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት ጀምሮ ባሉት ጊዜያት በሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ኮትዲቯር፣ አቢዬ፣ ዳርፉር፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ላይ በተደረጉ የሰላም ማስከበር ስራዎች  ተሳትፋለች፡፡

በአንዳንዶቹ ሀገራት ተልዕኮው አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስራ ላይ የዋለው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1948 ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ከሶስት ዓመት በኋላ በኮርያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋን አሀዱ ብላለች።

የሰላም ማስከበር ተልዕኮው በደርግ ዘመን ተቀዛቅዞ የቆየ ሲሆን፤ በሽግግር መንግስቱ ወቅት ኢትዮጵያ ብዙም ሳትደራጅ ለሩዋንዳውያን በመድረስ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋን እንደገና ማደስ ችላለች።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 12 ሺህ 500 የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በማሰማራት በዓለም ቀዳሚ ናት።