የስኳር በሽታ መድኃኒት አቅርቦት በህይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው - የስኳር ህሙማን

413
አዲስ አበባ ህዳር 5/2011 የ12 ዓመቷ ታዳጊ ማራኪ ጌታቸው በስኳር ህመም ከተያዘች አምስት ዓመት ሆኗታል፤ የሰውነቷን የስኳር መጠን ለማመጣጠንም መድሃኒት ትወስዳለች። ታዳጊዋ የስኳር በሽታ መድኃኒት አቅርቦት ጉዳይ በህይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንደሆነም ትናገራለች። የመድኃኒቱ በሚፈለገው መጠን አለመገኘት ጤንነቷን ስጋት ላይ እንደጣለውና በተለይም በመርፌ የሚወሰደው ኢንሱሊን በሚፈለገው ልክ አለመገኘት የስኳር መጠኗ እንዲዛባ እንደሚያደርገው ገልጻለች። የስኳር ህመሙን ተከትሎ በሰውነቷ ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር /ሆርሞን/ ኢንሱሊን ስለማያመነጭ ሰው ሰራሹ ኢንሱሊን በተገቢው ጊዜ ካልተወሰደ የሚያደርሰው የጤና ጉዳት አሳሳቢ እንደሆነም ተናግራለች። ማራኪ ጌታቸውና መሰሎቿን የሚያስታውሰው የዓለም የስኳር ህመም ቀን ለ28ኛ ጊዜ "የስኳር ህመም ይመለከተኛል" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በብሔራዊ ቲያትር በፓናል ውይይትና የሰውነት የስኳር መጠን ምርመራ በማድረግ ተከብሯል። ከስኳር ህመም ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መድኃኒቶች አቅርቦት ሊሻሻል እንደሚገባና ይህም ለታማሚዎች የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲያበጅለት ጠይቃለች። የ60 ዓመቱ አዛውንት አቶ መሐሪ ወልደ ማርያም እና የ65 ዓመቷ አዛውንቷ ወይዘሮ ዘገየሽ አሰፋ ከስኳር ህመም ጋር መኖር ከጀመሩ ስምንት እና ሃያ ዓመታትን እንዳስቆጠሩ ይናገራሉ። በበሽታው ምክንያት እግራቸውን ማጣታቸውን የተናገሩት አቶ መሐሪ መድኃኒቱን በሚፈለገው የምርት ዓይነትና መጠን ማግኘት ከባድ እንደሆነ ገልጸዋል። የመድኃኒቱ እጥረት በህሙማኑ ላይ እስከ ሞት የሚያደርስ የጤና እክል እንደሚያስከትል ተናግረዋል። ለስኳር ህሙማን መድኃኒቶች በነጻ አልያም የኢኮኖሚ አቅማቸው ታይቶ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ሊደረግ 'ቢደረግ' ሲሉም ጠይቀዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፋርማሲና የህክምና መሳሪዎች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የመድኃኒት ባለሙያው አቶ ሰለሞን አብደላ የስዊዘርላንዱ ኖቫርቲስት የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚያገለግሉ መድኃኒቶችን በዝቅተኛ ዋጋ ለማቅረብ ስምምነት ተፈርሞ ወደ ግዢ ሂደት መግባቱን ተናግረዋል። ሚትሮፊን የተሰኘውን የስኳር መድኃኒት ህሙማን በወር እስከ 25 ብር በመክፈል እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። ግዢው በመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በኩል የሚፈጸም በመሆኑ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ 'ይሰራጫል' ብለዋል። በኢትዮጵያ የኢንሱሊን መድኃኒት የሚከፋፈለው በኤጀንሲው በኩል በመሆኑ በቂ ባይሆንም ተመጣጣኝ ስርጭት እንዳለ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዱራዛቅ አህመድ በበኩላቸው የስኳር መድኃኒት የሚያቀርቡ የውጭ አገር መድኃኒት አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ 'ዋጋቸውን እንዲቀንሱ ጥረት ይደረጋል' ይላሉ። አዳዲስ የስኳር ህመም መድኃኒቶች እየገቡ ቢሆንም ተጠቃሚዎች አዲስ መድኃኒት የመጠቀም ፍርሃትና የለመዱትን የመምረጥ ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል። የመድኃኒቶቹ ፈዋሽነት የተረጋገጠ በመሆኑ ተጠቃሚዎች ያለባቸውን ፍርሃት ሊያስወግዱ እንደሚገባም መክረዋል። ከዓለም አቀፉ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን ጋር በመተባባር የስኳር ህመም ያለባቸው ሰባት ሺህ ህጻናት መድኃኒት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር አብዱራዛቅ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የስኳር ህመም ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ባለድርሻ አካላት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። እንደ ዓለም አቀፉ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን መረጃ በዓለም ላይ ከ420 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከህመሙ ጋር የሚኖሩ ሲሆን በሽታውን የመከላከልና መቆጣጠር ሥራ ካልተሰራ እ.አ.አ በ2020 የህሙማኑ ቁጥር በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል። በኢትዮጵያ በበሽታው ከተያዙ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች መካከል 90 በመቶው በሁለተኛው አይነት የስኳር ህመም የተያዙ ሲሆኑ የተቀሩት በአንደኛው ዓይነት በሽታ የተያዙ ናቸው። የተያዘው የህዳር ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ህመም የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ተብሎ ተሰይሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም