እየተወሰደ ያለው እርምጃ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል…..የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁራን

1402

አርባምንጭ ህዳር 5/2011 ከሙስናና ሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ እየተወሰደ ያለው እርምጃ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁራን ገለጹ፡፡

መንግስት ከሙስናና ሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ሰሞኑን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራን እርምጃው ሁሉም ሰው ከህግ በታች መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተቋሙ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ዮሐንስ ኃይሉ በሰጡት አስተያየት ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በዜጎች ላይ የተፈጸመው ድርጊት በዚህ ዘመን ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድርጊቱ ከህግ አንጻር ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሃይማኖትና ባህላዊ እሴት እንዲሁም ከሞራል አንጻር የሚወገዝ መሆኑንም ገልጸዋል ፡፡

“አገሪቱ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች አንጻር ሲታይ የተፈጸመው ድርጊት እንደማንኛውም ወንጀል የሚታይ አይደለም ” ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

“የህግ የበላይነትን ከማስከበር አንጻር ክፍተቶች አሉ ቢባልም የአገርና የህዝብ ሀብት መዝብረዋል፤ ኢሰብአዊ ድርጊትም ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዛቸው መንግስት በአሁኑ ወቅት ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያሳያል” ብለዋል፡፡

የወሰደው እርምጃ መንግስት የአገሪቱንና የዜጎችን ጥቅም ለአደጋ አሳልፎ እንደማይሰጥና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ እንደሚችል ህዝቡ እምነት እንዲጥልበት የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

” በጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጫ ተፈጸሙ የተባሉ የሙስና ወንጀሎችን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ በድሃ አገር ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ነው ” ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህሩ አቶ ደርሶልኝ የእኔአባት ናቸው ፡፡

የዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር ከመጣ ወዲህ የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ የአሁኑ እርምጃ ትልቅ መሆኑን ገልጸው በእዚህም “በሙስና የተዘፈቀው አካል አከርካሪው መመታት ጀምራል” ብለዋል ፡፡

“ይህ የመንግስት ጅምር ሥራ እንጂ መጨረሻ ባለመሆኑ በቀሪ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የሚፈጸሙ መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ” አቶ ደርሶልኝ ገልጸዋል ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሌላው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ጥበበ ሰሎሞን በበኩላቸው ግለሰቦቹ የፈጸሙት ድርጊት ከወንጀለኛ መቅጫ ህግና ከሙስና አዋጅ አንጻር ሲታይ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝና ክስ ሳይመሠረትባቸው በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያስገድዳል ፡፡

በሙስና አዋጁ መሠረት አንድ ሰው ከ10 ዓመት በላይ የሚያሳስር ድርጊት ፈጸሞ ከተገኘ የዋስትና መብቱ ላይከበርለት እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ህገ- መንግስታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ጠቅሰው የመንግስት ጅማሮ ውጤታማ እንዲሆን ህዝቡ ከመንግስት ጎን መቆም እንዳለበት አመልክተዋል፡፡