በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዛቸው የህግ የበላይነት መኖሩን እንደሚያሳይ የህግ ባለሙያዎች ገለጹ

77
መቀሌ ህዳር 05/ 2011 መንግስት በሌብነትና በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መያዙ በሀገሪቱ  የህግ የበላይነት መኖሩን በተግባር ያሳየ መሆኑን በመቀሌ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡ ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በሰብአዊ መብት ጥሰትና ሙስና  ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዛቸው ትክክል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የህግ ባለሙያዎቹ  የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ሰሞኑን ያወጣውን መግለጫ አስመልክተው እንዳሉት  የመንግስት እርምጃ ማንኛውም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን እንደማይችል ያስተምራል። የዜጎች  ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበር፣የመንግስትና የህዝብ ሃብትን ከታለመለት አላማ ውጭ ሲውል ተጠያቂነትን ሊኖር እንደሚችል ትምህርት የሚሰጥ ነው። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በዳኝነትና በጥብቅና ስራ የተሰማሩት  አቶ ጋይም ወልደጊዮርጊስ እንዳሉት ፣ ዲሞክራሲያዊ ህገመንግስት ባለበት ሀገር እንዲህ አይነት ጭካኔና ግፍ ይፈፀማል ብለው  ማመን እንደሚከብድ  ተናግረዋል፡፡ " መንግስት ባለበት አገር ህገመንግስት መሰረት ባደረገ መልኩ ሁሉም የሚተዳደርበት ሁኔታ እያለ ግለሰቦች ይህን ያህል ግፍ በግለሰቦችና በቡድኖች  ይፈፅማሉ የሚል እምነት አልነበረኝም፤ የግፍ ግፍ ሁኔታ ነው የሰማሁት" ብለዋል አቶ እስጢፋኖስ ገብሩ የተባሉት ሌላው የህግ ባለሙያ በበኩላቸው "የሙስና ወንጀልም ሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀመ አካል በህግ ተጠያቂ  የሚሆነው በፈፀመው ድርጊት እንጂ በማንነቱ ወይም በኃይማኖቱ ሊሆን አይገባም" ብለዋል። በጠቅላይ አቃቤ ህጉ የተሰጠው መግለጫ የግለሰቦችን ህገመንግስታዊ መብት ከመጣሱም አልፎ  ሂደቱን ለሚያየው የፍርድ አካል ተፅእኖ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ ተጠርጣሪዎችን አስቀድሞ ወንጀለኞች እንዲላቸው   የተደረገ በመሆኑ  ተገቢነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ ማንም ወንጀለኛ ከተጠያቂነት ማምለጥ እንደሌለበት የተናገሩት ደግሞ ሌላው የህግ ባለሙያ አቶ ፀሐዬ ጥላሁን ናቸው፡፡ ወንጀሉ ተፈፅመዋል የተባለው የበላይ አመራሮች በሚመሩዋቸው የመንግስት ተቋሞችና የስራ ክፍሎች መሆኑን አመልክተው ይህ ሆኖ  እርምጃው በአንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረና ፍትሃዊነት የጎደለው እንደሚመስል ተናግረዋል፡፡ አቶ ደስታ ተክሉ የተባሉት ነዋሪ በሰጡት አስተያየት እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ " እርምጃው የህግ የበላይነት ለማስከበር ከሆነ የሚደገፍ ነው " ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ኪሮስ ኃይሉ ናቸው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም