በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዛቸው ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ያለውን እምነት እንዲጨምር ያደርጋል-የባሌ ሮቤ ከተማ ነዋሪ

67
ጎባ ህዳር 5/2011 መንግስት በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዝ መጀመሩ ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ያለው እምነት እንዲጨምር እንደሚያደርግ በባሌ ሮቤ ከተማ የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡ ጉዳዩን በማስመልከት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት በወንጀል የተጠረጠሩ  ግለሰቦችን አጣርቶ ለህግ የማቅረብ ሂደቱ እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ መውረድ  አለበት፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት በከር አደም እንዳለው ህገ ወጦች ውስን የህዝብን ሀብት በመመዝበር ለግል ጥቅም ከማዋለቸውም በላይ ህዝቡ በመንግስት ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ መንግስት በብልሹ አሰራርና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውስጥ የተሳተፉ ተጠርጣሪ ግለሰቦችን አጣርቶ ለህግ ማቅረብ መጀመሩ አግባብነት ያለውና የሚደግፍ  ውሳኔ መሆኑንም ወጣቱ ተናግሯል፡፡ ''መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ብቻውን መወጣት አይችልም'' ያለው ወጣቱ እኛም ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ህገ ወጥነትንና ህገ ወጦችን በማጋለጥ ሂደት ግንባር ቀደም ሚናችንን እንወጣለን ብሏል፡፡ "ግለሰቦች የአገሪቱን ሀብት በዚህ ደረጃ ሲመዘብሩ የሚጠይቅ የመንግስት መዋቅር አለመኖሩ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው" ሲሉ የገለጹት ደግሞ የከተማዋ የሀገር ሽማግሌ  ሃጂ አሎ አደም ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪ  ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ የሚደገፍና አግባብነት  ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡   ''እርምጃው ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በመያዝ  የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት'' ብለዋል፡፡   አባ ገዳ ኢብራሂም ሱሩር በበኩላቸው  ዜጎች የአገራቸውን ሀብት መመዝበራቸው ከኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ ያፈነገጣና ሊወገዝ የሚገባው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡   መንግስት ተጠርጣሪዎችን ይዞ ለህግ በማቅረብ በሀገሪቱ  የሕግ የበላይነት እንዲኖር  ማድረግ መጀመሩ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል ።   አባ ገዳው እንዳሉት “መንግስት ሌቦችና አጥፊዎችን እንዲቀጡና በህግ እንዲጠየቁ በማድረግ በአገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ ለውጦች ፍሬ እንዲያፈሩ  ጉልህ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊደግፈው ይገባል“ ፡፡ ሌላዋ የከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አሽረቃ አደም በበኩላቸው ሲፈጸም የነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከሀገራችን ባህልና ወግ ጋር በእጅጉ የሚጣረስ ተግባር ነው በማለት ድርጊቱን አውግዘውታል ፡፡ በገዛ ዜጎቻችን የተፈጸመው አስነዋሪና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በሀብት ብክነትና ማህበራዊ ቀውስ ብቻ የሚቆም ሳይሆን አገሪቷ በአለም ህዝብ ዘንድ ያለትን በጎ ገጽታ ጥላሸት የሚቀባ እንደሆነ ወይዘሮዋ አስረድተዋል፡፡ ድርጊቱን በመፈፀም ተጠራጣሪ ግለሰቦች ላይ አስተማሪ የሆነ የህግ እርጃ መወሰድ እንዳለበት አስተያየት ሰጭዋ ጠቁመዋል፡፡ መንግስት የህዝብና የመንግስት ንብረትን ዘርፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ተከታትሎ መያዙ ለህግ የበላይነት መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተናገሩት አስተያየት ሰጭዎቹ  ሂደቱ  ህዝብን ባሳተፈ መልኩ እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን  በማውረድ የህዝብን እንባ ማበስ እንደለበት ጠቁመዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም