የመቀሌ ዩኒቨርስቲ አርሶ አደሩን ያሳተፈ የምርጥ ዘር መረጣና ብዜት እያካሄደ ነው

78
መቀሌ  ህዳር 4/2011 የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የሰብል የምርጥ ዘር አቅርቦት  ስርአት ለማጠናከር አርሶ አደሮች ያሳተፈ ምርጥ ዘር የመረጣና ብዜት ስራ እያከሄደ መሆኑን ዩኒቨርስቲው አስታወቀ፡፡ በዩኒቨርስቲው የተቀናጀ የምርጥ ዘር ልማት ፕሮጀክት ከ3ሺህ400 በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አላማ በክልሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰብል ምርጥ ዘር አቅርቦት ስርዓት ለማጠናከር መሆኑን  በዩኒቨርስቲ የተቀናጀ ምርጥ ልማት ፕሮጀክት የአርሶ አደሮች አደረጃጀት ባለሙያ አቶ ሰሎሞን ጴጥሮስ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ የምርምር ተቋማት የወጡ የሰብል ምርጥ ዝርያዎች ለአምራቹ  ከመለቀቁ በፊት በተወሰኑ አርሶ አደሮችን ማሳ ላይ ለሶስት ዓመታት ያህል የሙኮራ ስራ እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡ "አርሶ አደሮች ለአካባቢያቸውን የሚስማማ  ዘር ከመረጡ በኋላ  ወደ ማባዛት ስራ እንዲሸጋገሩ ይደረጋል "ብለዋል፡፡ ባለሙያው እንዳመለከቱት አርሶ አደሮቹ ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ሁለት ዓመታት እንዳስቆጠረ ጠቁመው በሚቀጥለው ዓመት አርሶ አደሮች ለአካባቢያቸው የሚስማማ ምርጥ ዘር በመለየት የማባዛት ስራ እንደሚያከናውኑ አስረድተዋል፡፡   በምርጥ ዘር መረጣና ማባዘት ስራ ከሚሳተፉ አርሶ አደሮች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሴቶች እንደሆኑ የተናገሩት ደግሞ በፕሮጀክቱ የስርዓተ ጾታና ገጠር ልማት ባለሙያ ወይዘሮ  አዝመራ ወልደዝጊና ናቸው፡፡   እንደባለሙያዋ ገለጻ ሴት አርሶ አደሮች ግማሽ እንዲሆኑ የተደረገበት ምክንያት በምርጥ ዘር ጥበቃና አቅርቦት ከፍተኛ ድርሻ  ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡   በትግራይ ክልል ዘጠኝ ወረዳዎች በሚካሄደው የመረጠና ማባዛት ስራ የተካተቱት  ዝርያዎች ስንዴ፣ገብስ፣ዳጉሳ፣ጤፍ፣ሰሊጥና ሽምብራ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡   "አርሶ አደሩ ለመምረጥ እንዲያመቸው ከአንዱ የሰብል ዓይነት በርካታ  ዝሪያዎች እንደቀርቡለት ይደረጋል "ብለዋል፡፡   ባለሙያዎቹ እንዳሉት እስካሁን ባለው የሙከራ ስራ ጤፍ የተለምዶው 12 ኩንታል የነበረው ወደ 20 ስንዴ ደግሞ ከ10 ወደ 20 ኩንታል ከፍ ማድረግ ተችሏል   በፕሮጀክቱ ከተቀፉ አርሶ አደሮች መካከል በእንደርታ ወረዳ የድድባ ቀበሌ   አርሶ አደር ሞላ አብረሀ በሰጡት አስተያየት በፕሮጀክቱ ከተሰጣቸው ሶስት የስንዴ ዝሪያዎች በምርት አያያዙና ለአካባቢው የሚስማሙ መረጣ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአሁን በፊት ከምርምር የወጡ ምርጥ የዳቦ ስንዴ በመጠቀም ከግማሽ ሄክታር መሬት 20 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡ "ይህም ቀደም ሲል ሲጠቀሙበት የነበረው " ሸሓን"   የአካባቢው ስንዴ በምርታማነቱ በእጥፍ ብላጫ አለው "ብለዋል፡፡ ሶስት የስንዴ ዝሪያ ተሰጥትዋቸው የተሻለው ለመምረጥ ለሁለት ዓመታት በሙከራ ላይ እንዳሉ  የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ቀበሌ  ሴት አርሶ አደር መንጸገባ ህንደያ ናቸው፡፡ ምርጥ ዘርና የምርት ማሳደጊያ ግብአት የመጠቀም ባህላቸው እያደገ በመምጣቱ ምርጥ ዘር አበዝቶ መሸጥ አዋጪ እንደሆነ መረዳታቸውን   ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም