ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የ2018 ምርጥ ሴት ታዳጊ አትሌት ለመባል ከመጨረሻዎቹ አምስት ዕጩዎች ተካተዋል

95
አዲስ አበባ ህዳር 4/2011 ኢትዮጵያዊያኖቹ አትሌቶች መሰረት በለጠና አትሌት መስከረም ማሞ የ2018 ምርጥ ታዳጊ ሴት አትሌት ለመባል ከመጨረሻዎቹ አምስት ዕጩዎች ውስጥ ተካተቱ። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዛሬ ይፋ ባደረገው የ2018 ምርጥ ታዳጊ ሴት አትሌት የመጨረሻዎቹ  አምስት ዕጩዎች ውስጥ ሁለቱን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ማካተቱን አስታውቋል። አትሌት መሰረት በለጠ በ2018 በተሳተፈችባቸው ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድሮች ላይ ስኬታማ ውጤት አስመዝግባለች። አትሌቷ በ2018 በሞሮኮ በተካሄደው ሳፊ ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን፣ በስዊድኑ የጎትቦርግስቫርቬት የግማሽ ማራቶንና በዴንማርኩ የኮፐንሀገን የግማሽ ማራቶን አሸናፊ ሆናለች። በተጨማሪም በስፔን ቫሌንሺያ ከተማ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ተሳትፋ ስድስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በሌላ በኩል በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች የምትወዳደረው አትሌት መስከረም ማሞ በ2018 በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ስኬታማ ጊዜ አሳልፋለች። በፈረንሳይ ሞንድቪል ከተማ በተካሄደ የቤት ውስጥ የ2 ሺህ ሜትር ውድድር እንዲሁም በፊንላንድና ጣልያን በተካሄዱ የ3 ሺህ ሜትር ውድድሮች ላይ አሸንፋለች። በኳታር ርዕሰ መዲና ዶሃ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ በ3 ሺህ ሜትር ውድድር ሰባተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል። በውድድር ዓመቱ በሌሎች የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይም መልካም የሚባል ውጤት አስመዝግባለች ለሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተጨማሪ ጃማይካዊቷ የአጭር ርቀት ሯጭ ብሪያና ዊሊያምስ፣ አሜሪካዊቷ የአጭር ርቀት የመሰናክል ውድድሮች ሯጭ ሲዲኒ ማክላኡግሊንና እና ኬንያዊቷ የ3 ሺህ ሜትር መሰናክር ተወዳዳሪ ሴሊፒን ቼፕሶል የመጨረሻ እጩዎች ውስጥ የገቡ አትሌቶች ናቸው። በወንዶቹ አትሌት ሰለሞን ባረጋ የ2018 ታዳጊ አትሌቶች የመጨረሻ እጩዎች መካተቱ ይታወቃል። የ2018 ምርጥ ታዳጊ አትሌት አሸናፊዎች ህዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ ሞናኮ በሚደረገው የዓለም የዓመቱ የአትሌቶች ሽልማት ይፋ እንደሚሆን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል። ማህበሩ በሁለቱም ጾታዎች ለታዳጊ አትሌቶች ሽልማት የሚሰጠው እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶችን ለማበረታት እንደሆነ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም