ብራዚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ትፈልጋለች - ተሰናባቹ አምባሳደር ኦክታቪዎ ሄንሪክ ኮርቴስ

91
አዲስ አበባ ጥቅምት 4/2011ብራዚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደምትፈልግ ተሰናባቹ በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ኦክታቪዎ ሄንሪክ ኮርቴስ ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ተሰናባቹን አምባሳደር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። አምባሳደሩ በቆይታቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲጠናከር ላደረጉት አስተዋጽኦ ሚኒስትር ዴኤታው አመስግነው፣ ኢትዮጵያ ከብራዚል ጋር በግብርና፣ በሃይል አቅርቦትና በስኳር ኢንዱስትሪ መስኮች ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍ ማድረግ እንደምትፈልግም ገልጸዋል። በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይም ከብራዚል ጋር መስራት ለአገራችን ጠቃሚ መሆኑን አውስተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ብራዚል የቀጥታ በረራ ማድረጉ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ያጠናከረው መሆኑንም አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ አመልክተዋል። ኢትዮጵያ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ መስክ ላይ እያካሄደቸው ያለውን እምርታዊ ለውጥ በመጠቆም ከኤርትራ ጋር ያለው ሁሉን አቀፍ ትብብር ለቀጠናው ሰላም ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል። አምባሳደር ኦክታቪዎ ሄኔሪክ ኮርቴስ በበኩላቸው ከኤርትራ ጋር የተደረገው መልካም ግንኙነት ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በመጠቆም አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ከነበረው በላይ ለማጠናከር ፍላጎት ያላት መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከብራዚል ጋር መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረችው እ.ኤ.አ. በ1961 መሆኑን ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያና ብራዚል በግብርና፣ በሰላም ማስከበር፣ በዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድና በመሰረተ ልማት መስክ ጠንካራ ትብብር አላቸው። ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚው መስክ ያላቸው ትስስር ዝቅተኛ ሲሆን አገራቱ ይሄን በመገንዘብ ያለውን የንግድ ልውውጥ መጠን ለማሳደግ ከሁለት ዓመት በፊት የንግድና ኢንቨስትመንት የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። ስምምነቱ የተፈረመው የቀድሞው የብራዚል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው። የብራዚል መንግስት በአገሩ የሚገኙ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በግብርናና መሰረተ ልማት እንዲሰማሩ እንደሚያበረታታ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጽ ቆይቷል። ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድን በተመለከተ ብራዚል በሰሜን ኢትዮጵያና በአዲስ አበባ የቆሻሻ አወጋገድ ፓይለት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም