ከ23 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ በአዲስ አበባ ከሶማሊያ አቻው ጋር ይጫወታል

53
አዲስ አበባ ጥቅምት 4/2011 የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዞን የኦሊምፒክ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ነገ ከሶማሊያ አቻው ጋር ያደርጋል። በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድር ለመሳተፍ የሚያደርገው የማጣሪያ ጨዋታ ነገ ከቀኑ በ10 ሠዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል። በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ ከጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን በአዲስ አበባ ስታዲየም አካሂዷል። ቡድኑ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ከሱዳኑ አል ሒላል ኦቢዬድ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 2 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል። የሶማሊያ የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ የመልስ ጨዋታው ከህዳር 9-11 ቀን 2011 ዓ.ም በጅቡቲ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የስቴዲየም መግቢያ ዋጋ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መደበኛ ዋጋ መሠረት እንደሆነ ፌዴሬሽኑ አሳውቋል። በአዲስ አበባ ስቴዲየም የሚደረገውን የኢትዮጵያና ሶማሊያ ጨዋታ ቱኒዚያዊያኑ ጉዊራት ሀይተም በመሐል ዳኝነት፣ ረምዚ ሔርች እና ኸሊል ሀሰን በረዳት ዳኝነት ይመሩታል። ኢትዮጵያ በድምር ውጤት ሶማሊያን ካሸነፈች በመጋቢት 2011 ዓ.ም ከማሊ ብሔራዊ ቡድን ጋር ትጫወታለች። ማሊን አሸንፋ ወደ ቀጣዩ ዙር ካለፈችም በመጨረሻው ዙር ከሩዋንዳ፣ ሞሮኮና ዴሞክራቲክ ኮንጎ አንዳቸውን ታገኛለች። ይህን ዙር ካለፈች ደግሞ በታህሳስ 2012 ዓ.ም በግብፅ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ አገሮች የኦሎምፒክ ውድድር የምትሳተፍ ሲሆን በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ከወጣች ለቶኪዮ የእግር ኳስ ውድድር በቀጥታ ታልፋለች። በኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድሩ ለመሳተፍ ረጅም ጉዞ የሚጠይቅ ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑም ከተጋጣሚዎቹ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ይገመታል። ጃፓንን ጨምሮ 16 አገሮች በሚሳተፉበት የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከአፍሪካ አህጉር በወንዶች እግር ኳስ ሶስት አገሮች ይወከላሉ። እ.አ.አ በ2020 በጃፓን ርዕሰ መዲና ቶኪዮ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታ የእግር ኳስ ዘርፍ በአህጉራት ተከፋፍለው በሚደረጉ ከ23 ዓመት በታች ውድድሮች በሚመዘገቡ ውጤቶች መሰረት አገሮች ለውድድሩ የሚያልፉ ይሆናል። የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፊፋ በኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድሩ የሚሳተፉ አገሮች ዕድሜያቸው ከ23 ዓመት በላይ የሆኑ ሶስት ተጫዋቾችን መምረጥ እንደሚችሉ በውድድሩ ደንብ ላይ አስቀምጧል። የኢትዮጵያ ወንዶች ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድሮች ለመሳተፍ በተለያዩ ጊዜያት የማጣሪያ ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን እ.አ.አ በ2004 በአቴንስ  እ.አ.አ በ2008 በቤጂንግ አሎምፒክ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን አድርጎ ሳይሳካለት ቀርቷል። ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1956 በአውስትሪሊያ ሜልቦርን ኦሎምፒክ የእግር ኳስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታ ማድረጓን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም