በወንጀል የተጠረጠሩ መያዛቸው ለህግ የበላይነት መከበር የላቀ አስተዋጽኦ አለው ፡- አስተያት ሰጪዎች

64
ጊምቢና አምቦ ህዳር 4/2011 መንግስት በሌብነትና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዙ ለህግ የበላይነት መከበር የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው   በጊምቢና አምቦ  ከተሞች አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት በወንጀል  የተጠረጠሩ  ግለሰቦቹን  ለህግ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል  አቶ ዘርይሁን ጉዲና በሰጡት አስተያየት  የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን የሰጡትን መግለጫ መከታተላቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግስት የህዝብና የመንግስት ንብረትን ዘርፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ተከታትሎ መያዙ ለህግ የበላይነት መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል። እንደአስተያየት ሰጪው ገለጻ መንግስት በህግ ጥላ ስር የነበሩ ታራሚዎችን  በማሰቃየት የሰብዓዊ መብታቸውን ጥሰዋል የተባሉት ግለሰቦች እንዲያዙ መድረጉ  ተገቢ ነው። የከተማዋ የሀገር ሽማግሌ አቶ ኃይሌ ሪቅቱ በበኩላቸው መንግስት በወንጀል በተጠረጠሩ ግልሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ አንዱ የለውጡ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ዜጎችም ሁል ጊዜ  የሚተማመኑበት ስርዓት እንዳላቸው እንዲገነዘቡ በማድረግ በኩል ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት በሌብነት የጠረጠራቸውን የሜቴክ ኮርፖሬሽንን የቀድሞ ስራ ሃላፊዎችና ባልደረቦችን በመያዝ  ምርመራ መጀመሩ የለውጡ አንዱ አካል መሆኑን እንደሚረዳ  የገለጸው ደግሞ ወጣት ተመስገን ታፈሰ ነው፡፡ እርምጃው ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳዶ በመያዝ  የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ  የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ተጠናክሮ  መቀጠል እንዳለበት አመልክቷል። ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አንሻ አሊ በበኩላቸው  በየማረሚያ ቤቱ ይደረግ የነበረው አሰቃቂና አስነዋሪ ተግባር ለጆሮ የሚከብድና ኢትዮጵያዊነትን የማይወክል በመሆኑ በፈፃሚዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት ሊተላለፍ ይገባል ብለዋል ። በተመሳሳይ ከአምቦ ከተማ  ነዋሪዎች መካከል የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ፈየራ አያና በሰጡት አስተያየት የሕግ የበላይነትን በመጣስ በህዝቦች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያደረጉ አካላት መያዛቸው  ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "ሌቦችና አጥፊዎችም እንዲቀጡና በህግ እንዲጠየቁ በማድረጉ ለውጡ የሁሉም አካል ነው "ብለዋል፡፡ በየደረጃውም የሀገሪቱን ሀብት በመስረቅ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ በርካታ ግለሰቦች ስለሚኖሩ መንግስት የጀመረውን በህግ አግባብ መጠየቅ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ ወጣት ነገራ ኢተፋ በበኩሉ በሀገሪቱ ይህን ያህል ጭካኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸማል ብሎ አስቦት እንደማያውቅ ገልጿል፡፡ ማንኛውም ጥፋተኛ ወንጀል ፈጽሞ ቢገኝ መጠየቅ ያለበት በህግና በሕግ አግባብ ብቻ ሆኖ ሳለ በዜጎች ላይ አረመኔያዊ ድርጊት መፈጸም ተገቢ አለመሆኑንም ወጣቱ ተናግሯል፡፡ ሆኖም መንግስት አሁን በጀመረው የህግ አግባብ ተጠርጣሪዎችን ይዞ ለህግ በማቅረብ በሀገሪቱ  የሕግ የበላይነት እንዲኖር  ማድረግ መጀመሩም የሚደነቅ ነው ብሏል፡፡ ወጣቱም ለረጅም ጊዜ ሲጠይቅ የነበረው የህግ የበላይነት ተግባራዊ እየሆነ መመልከቱ የለውጡ አካል እንዲሆንም ጭምር የሚያደርገው መሆኑን ገልጿል፡፡ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ የትምህርት ዘርፍ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነችው ሴና ጭምዲ "ሲፈጸም የነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከሀገራችንን ባህል፣ እምነትና ወግ በእጅጉ የሚጣረስ ነው" ብላለች፡፡ ድርጊቱን የፈፀሙ   ግለሰቦች መያዛቸው በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እየተረጋገጠ ስለ መምጣቱም አንዱ ማሳያ እንደሆነም አስተያየት ሰጪዋ ተናግራለች፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም