ከስደት መልስ…

102
አስማረች አያሌው/ኢዜአ/ ከአንድ ትምህርት ቤት ደጃፍ ለተማሪዎች በረዶ የምትሸጠውን  ወጣት  በአይን ሳውቃት ጊዜው ትንሽ ረዘም ይላል። ከልጅነቷ ታታሪነት የማይለያት ወጣት ጫማ ስታስውብም አስታውሳለሁ፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ከእሷ ጋር ለማውራት እድል ገጥሞኝም ነበር።ወጣቷ የአእምሮ ህክምና እየተከታተለች መሆኑን ነገረችኝ፤ ሲያዩዋት ሙሉ ጤነኛ ብትመስልም ለዚህ ችግር የዳረጋትን ምክንያት ጠየኳት፡፡ “ለአንድ አመት ገደማ አረብ ሃገር ነበርኩ፤ ጥሩ ሰዎች አላጋጠሙኝም፣ፎቅና ምድር የሆነውን ቤት ግድግዳ ሳይቀር እንዳጥብ ያደርጉኛል። መኪና ማጠብም ስራዬ ነው፤ ከዚህ ሁሉ ከባድ ስራ በኋላም በቂ ምግብ አይሰጠኝም፣ወይ አንድ ዳቦ ይወረውሩልኛል፤ ይህ ሳያንስ ከቤት እንዳልወጣና ከሰው እንዳልገናኝ ስለሚያደርጉኝ  ለአእምሮ ችግር ዳረገኝ” ትላለች፡፡ ስደት ለመሄድ የወሰነችበትን ምክንያት እንደነገረችኝ “ዘጠነኛ ክፍል ስወድቅ ተናደድኩና ለመሄድ ወሰንኩ ካዛ በፊት የመኪና ረዳት ሆኜ እየሰራሁ ገንዘብ አገኝ ነበር ሙሉ ጤነኛም ነበርኩ”ነው ያለችው። ወደ ሃገር ቤት ስትመለስ አእምሮዋ ታውኮ እራሷን እንኳን በአግባቡ አለማወቋን የተናገረችው ወጣቷ፤ ህክምና በመከታተል የጤናዋ ሁኔታ እየተሻሻለ መሆኑና ጉዳቱ ግን  በአእምሮዋ ብቻ ሳይወሰን ለወገብ ህመም ዳርጓት እንዳለፈ ነው የገለፀችው፡፡ ሌላዋ ከስደት ተመላሽ ወጣት መሰረት ዘርጋው የስደት ህይወቷ የሚጀምረው ከ10 አመት በፊት ወደ ሶሪያ በመሰደድ እንደነበር ትናገራለች። ከሃገር ስትወጣም በደላላ እንደነበር የምትገልፀው መሰረት ጥሩ የሥራ ሁኔታ “አላጋጠመኝም” ትላለች፡፡ በሶሪያ አንድ ዓመት ከስምንት ወር ቆይታ ያደረገችው ወጣቷ በወር  የሚከፈላትን 8 መቶ የኢትዮጵያ ብር እንኳን  በስርዓት እንደማይሰጧት ታስታውሳለች።  ባለችበት ህንፃ ላይ አንዲት ልጅ ተገላ በማየቷ  "እኔንም ይገሉኛል"  በማለት ፈርታ ወደ ሃገሯ መመለሷን ነው ያወጋችን፡፡ በዚህ ያላበቃው የስደት ህይወቷ ጓደኞቿ ”አሁን ቋንቋ ችለሻል” ብለው ወደ ባህሬን በደላላ እንድትወጣ እንዳደረጓት ትገልፃች። “ባህሬንም ጥሩ አልገጠመኝም፤ ሶስት አመት ሙሉ ያለደሞዝ በግዞት አሳልፌያለሁ፤ከቤት ያለመውጣትና የማያቸው ክፉ ድርጊቶችም ለጭንቀት በሽታ ዳርገውኛል  ” ትላለች፡፡ የባህሬን መንግስት ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸው ዜጎች ከሃገር እንዲወጡ ሲያዝ አሰሪዋ ባደረባት ስጋት  ያለምንም ጥሪት ወደ ሀገሯ  እንደመለሰቻት ተናግራለች። “ሁኔታዬን የተመለከቱ ሰዎች አየር መንገድ ላይ የተወሰነ ገንዘብ አዋተው ሰጡኝ፤ እራሴንም  የማላውቅበት ሁኔታ በመኖሩ ወደ ሃገር የገባሁት በባዶ አግሬ ነበር” ስትልም ነው በምሬት የገለፀችው። ወደ ሃገር ከገባች በኋላ በተደረገላት ህክምና  የጤንነቷ ሁኔታ ተሻሽሎ ወደ ሥራ ለመሰማራት የሚያስችላት  የሙያ ስልጠና  መከታተሏንም ተናግራለች፡፡ ከስራ እድል ፈጠራ አኳያ የስደት ተመላሾች ትዝብት   እነዚህ ስደተኞች ገና ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የሥራ እድል እንደሚመቻችላቸው የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ቃል በመግባት፤ የስነልቦናና የሙያ ስልጠና እንደሰጧቸው ያናገርናቸው  ተመላሾች አልሸሸጉም። ግን ደግሞ ሥልጠና ከተሰጣቸው በኋላ የት አላችሁ ብሎ የሚጠይቃቸው አካል እንዳልነበረም ነው የገለፁት። ወጣት መሰረት ስለ ሁኔታው ተጠይቃ በወሰደችው የንግድ ክህሎት ስልጠና ወደ ስራ መግባት አለመቻሏንና ተደጋጋሚ የቦታ ጥያቄ ብታቀርብም ምላሽ ማጣቷን ነው  የምትገልጸው፡፡ “ከስልጠናው በኋላ ቦታ እንደሚሰጥ የተገባን ቃል በተግባር አላገኘሁትም” ያለችው ወጣቷ አሁን ላይ ህይወቷን የምትመራው የቀን ስራ እየሰራች መሆኑን ተናግራለች ፡፡ በተለይም ማረፊያ ቤት የሌላት በመሆኑ  በሌላት ገቢ ለቤት ኪራይ ወጪ መዳረጓን ጠቁማ “ጎዳና ላለማደርና ተጨማሪ ችግር ላለማምጣት የቀን ስራ እየሰራሁ በወር አንድ ሺህ ብር የቤት ኪራይ  እከፍላለሁ፤ ችግሩ በዚህ ሳያበቃ አንድ ቀን የቤት ኪራይ ባሳልፍ እቃዬን አውጥተው በረንዳ ላይም ጥለውታል” ስትል ተናራለች፡፡ አሁን ላይ ሁለት አማራጮችን እያሰበች እንደሆነ  የምትገልፀው መሰረት “በሃገሬ ላይ ሰርቼ መኖር ካልቻልኩና ከችግር ካልወጣሁ  በህይወቴ  ቆርጬ ተመልሼ ወደ አረብ ሃገር እሄዳለሁ “ነው ያለችው፡፡ ሌላኛዋ ከስደት ተመላሽ ህይወት ወንድሙ በህጋዊ ሽፋን ወደ ሳውዲ ብትሄድም የመኖሪያ ፍቃድ ባለማግኘቷ ወደ ሃገሯ ተመልሳለች፡፡ “መንግስት ወደ ሃገር ግቡ ሲለን ሁሉን ነገር  አመቻቻለሁ ብሎ ነበር” የምትለው ህይወት የምግብ ስራ ስልጠና ወስዳ  ሥራ ለመጀመር በራሷ የምታደርገው ጥረት አለመሳካቱን ገልፃ የሚመለከተው አካል “የት ደረሳችሁ ብሎ ሊያየን ይገባል” ብላለች፡፡ “ከምንሰራበት ሃገር በድንገት በመውጣታችን የራሳችንን ስራ ለማቋቋም ይከብደናል” ያለችው ህይወት ለስራ ጀማሪ የቦታ፣ የግብር እና የስራ መነሻ ካፒታል ሟሟላት አዳጋች መሆኑን ነው የገለፀችው፡፡ ሌላው የሳውዲ ተመላሽ  በድሩ አደም ከ16 አመት በፊት በህጋዊ ሽፋን ሥራ ፍለጋ ከአገር ወጥቶ በየአመቱ ለደላሎች 9ሺህ ሪያል በመክፈል የመኖሪያ ፍቃድ በማደስ ይኖር እንደነበር ነው ያስታወሰው፡፡ የሳውዲ የውጡልኝ ጥያቄን ተከትሎ ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ባለመያዙ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ሃገሩ ተመልሷል፡፡ ወደ ሃገር ከተመለሰ በኋላ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ የተሰጡ ስልጠናዎች “የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እንድረዳ አስችሎኛል” ያለው በድሩ የንግድ ስራ ስልጠና መከታተሉንም ሳይጠቁም አላለፈም፡፡ ከስልጠና በኋላም 12 ሆነው ለንግድ ስራ እንደተደራጁ ያስታወሰው በድሩ በተለያየ ምክንያት ባለመስማማታቸው ቁጥራቸው ወደ 6 መቀነሱና  ሁሉንም ኃላፊነት ለእሱ ብቻ ስለተውት በግል ለመደራጀት በመወሰን  የንግድ ቦታ ሼድ እንደተሰጠው ተናግሯል፡፡ “የተሰጠኝ ሼድ ለንግድ ስራ አመቺ ባለመሆኑ እስካሁን ስራ አልጀመርኩበትም” ያለው በድሩ ሼዱ ለመንገድ ጀርባውን የሰጠ፣ በላሜራ የተደፈነና ለንግድ ስራ የማይጋብዝ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በቀጣይ በአንፃራዊነት የተሻለ የንግድ ቦታ ለማግኘትም ጥያቄውን መቀጠሉን አልሸሸገም፡፡ ”በሃገር ሰርተን እንለወጣለን ስንል የተንዛዙ አሰራሮችንና አላስፈላጊ ምልልሶችን መንግስት ሊያስወግድ ይገባል” ብሏል፡፡ ለዚህም ማሳያው  ስድስት ሆነው  የተደራጁትን ወደ ግል ኢንተርፕራይዝ ለማዞር ከስድስት ወር ያላነሰ ግዜ እንደፈጀበት፣ በየወረዳው ሰው አገልግሎት ሲጠይቅ ከፎቶ ኮፒ ማሽን አቅም ተበላሽቷል፤ ውጪ አስነስተህና መባሉና የህብረተሰቡን ጥያቄ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ከማቅረብ ይልቅ መመሪያው አይፈቅድም፤ አልያም አልወረደም የሚሉ ምክንያቶችን መሰንዘሩ አግባብ አለመሆኑን ነው የገለፀው። “ከ12 አመት በፊት ከሃገር ከወጣሁ በኋላ የሳውዲ መንግስት ውጡ እስኪል ሳልመለስ በመቆየቴ የሃገሪቱን ለውጥ አልተገነዘብኩም ነበር”  የምትለው ሌላዋ ከስደት ተመላሽ  የትናየት ታደሰ  በወቅቱ ስደት የሚጠላ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ የሚሰራበት  ሁኔታ ነበር ትላለች፡፡ አሁን አሁን ግን  የህገወጥ ስደት ከመጠን በላይ መበራከት የባህር ላይ ሞቱ፣ የርስ በርስ መጨካከን እየታየ መምጣቱን  ነው የምትገልጸው፡፡ ከስደት መልስ በተመቻቸላት የመንጃ ፍቃድ ስልጠና  ሙያውን እንደቀሰመች የምትናገረው የትናየት ስልጠናውን አጠናቃ ፍቃዱን ብታገኝም ቀጣሪ ድርጅት ማጣቷን ነው የጠቆመችው፡፡ “ማስታወቂያ ብከታተልም ሁሉም ቢያንስ  የሁለት አመት ልምድ የሚጠይቁ ናቸው፤አሁን ቢያንስ መጠነኛ ስልጠና ሰጥቶ የሚቀጥረኝ ድርጅት ባገኝ ደስተኛ ነኝ” ብላለች፡፡ የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምን ይላል? በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የውጪ ሃገር የስራ ስምሪት ቁጥጥርና ክትትል ባለሙያ አቶ ብሩክ የሺጥላ እንደሚሉት  ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በቢሮው ተመዝግበው ስልጠናና የስራ እድል ሲመቻችላቸው የነበሩ 2061 ተመላሾች ናቸው፡፡ በተለይም  በኮንስትራክሽንና ማምረቻ ዘርፍ ከተሰማሩ የግሉ ሴክተር ጋር በመተባበር  አብዛኞቹን  “ስራ አሲዘናል”  ነው ያሉት አቶ ብሩክ  አሁንም ወደ ስራ ላልገቡ ተመላሾች ስራ ለማስያዝ ቢሮው የማያቋርጥ ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ “ተመላሾች ሁሉንም ነገር መንግስት ያመቻቻል ብለው መጠበቅ አይገባቸውም” ያሉት አቶ ብሩክ በራሳቸው ጥረት ለሚያገኝዋቸው የስራ እድሎች ቢሮው ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የትብብር ደባዳቤ እንደሚፅፍ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ስለ ጉዳዩ ምን ይላል? በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ የስራ አድል ፈጠራ ዘርፎች ቡድን መሪ አቶ ነብዩ ውድነህ እንደሚሉት በልዩ ትኩረት ድጋፍ ከሚደረግላቸው መካከል የስደት ተመላሾች እንደሆኑ ነው።፡፡ “ሆኖም የተመላሾች የስራ ዘርፍ አመራረጥ  ውጤታማ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ነው” ይላሉ፡፡ የግል ባለሃብቱ የሚረባረብበት የንግድና የአገልግሎት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት መጠየቅ ከውድድርም አኳያ የሚበረታታ አለመሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ለካፍቴሪያ አገልግሎት ሰፋ ያለ ፊት ለፊት ቦታ እንደሚጠይቅ ሁሉ ከተማዋ ማቅረብ የቻለቻቸው ሼዶች ደግሞ ማምረቻን ታሳቢ አድርገው የተሰሩና ከመንገድ የወጡ ናቸው ይላሉ፡፡ በንግድ ዘርፍ የሚሰማሩም ሃገሪቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ስራዎች ከምታበረታታው የሃገር ውስጥ ምርት ሽያጭ  በተጻራሪ የውጪ ሃገራት ምርቶችን ለመሸጥ ታሳቢ የሚያደርጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ተመላሾች ወደ ሚፈለገው የማምረት ዘርፍ እንዲመጡ የማግባባት ስራ ይሰራል ያሉት አቶ ነብዩ ወደ ማምረቻው ዘርፍ እንዲመጡ ተጨማሪ ስልጠና እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡ ከተማዋ በያዝነው በጀት አመት የስራ እድል ከምትፈጥርላቸው 161 ሺህ 106 ሰዎች ከስደት ተመላሾች በልዩ ትኩረት እንደሚስተናገዱም  ተናግረዋል፡፡ እንደ ማጠቃለያ በህገወጥ ስደት ምክንያት የሚደርሱ አስከፊ የአካል ጉዳቶችና ሞት የየቀን ዜናም ቢሆኑ ዜጎች በህይወታቸው ቆርጠው በህጋዊ ሽፋንና በህገወጥነት ሀገራቸውን ጥለው አየተሰደዱ ነው። እንደ ገፊ  ምክንያት  ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው የሚለወጡበት እድል መጥበቡ እና ህጋዊ የውጪ ሃገር  የስራ ስምሪት በሚፈለገው ፍጥነት አለመሄዱ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ያገኘነው መረጃ  ደግሞ በህጋዊ መንገድ ለመሄድ ጅምር ሥራዎች መኖራቸውንም ነው የጠቆሙት።በዚህም በህጋዊ መንገድ ወደ ተፈቀዱ የአረብ  ሀገራት ለመሄድ በመጀመሪያ ዙር የሙያ ስልጠና ወስደው ብቃታቸውን ያረጋገጡ 350 ሰዎች በቅርቡ እንደሚመረቁም ነው የጠቀሱት፡፡ ከህጋዊ ኤጀንሲዎች ጋር በመገናኘት ቀጣይ ሄደቱን እንደሚጀምሩና በመንግስት በኩል የሰራተኞችን ደሞዝ የመወሰን እና መሰል የህጋዊነት ስራዎች ከቀጣሪ ሃገራት ጋር እየተሰራ መሆኑን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ሁሉም  ዜጋ  በሀገሩ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በመረዳት ተደራጅቶም ሆነ በግሉ  መስራት የሚችልበት ሁኔታዎች ሊመቻች ይገባል።ሁለተኛው አማራጭ በሌሎች ሀገራት ሰርቶ መለወጥ የሚፈልግም ቢሆን ህጋዊ መንገድን ብቻ ምርጫው በማድረግ ወደ ፈለገበት ሀገር  ሄዶ መስራት የሚችልበትን ሁኔታ የሚመለከተው አካል በማመቻቸት ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። ዜጎችን አታለው  የሚያስኮበልሉ ህገወጦችም አደብ ሊገዙ ይገባል ባይ ነን።   ሰላም!
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም