የሐረሪ ክልል መንግሥት የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የአመራር ለውጥ እንደሚያደርግ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታወቁ

99
ሐረር ህዳር 3/2011 የሐረሪ ክልል መንግሥት ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎችን ለመመለስ የአመራር ለውጥ እንደሚያደርግ አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ከክልሉ አመራር አካላት ጋር በወቅታዊ ገዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ አዲሱ አመራር በትጋት ይሰራል። የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና አድሏዊ አሰራሮችን መከላከል ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት ይሆናሉ ብለዋል። እንዲሁም በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚታዩ ችግሮች ለመፍታትም እንደሚሰራ አቶ ኦርዲን አመልክተዋል። በተጨማሪም የከተማ ጽዳትና ውበትና የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮች፣ የመኖሪያ ቤትና ጥያቄዎችና አቅመ ደካማ አረጋውያንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል። ተጠያቂነትና አገራዊ አንድነትን በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለዚህም አመራሩ የ100 ቀናት ዕቅድ በማውጣት ተጨባጭና ለውጥ ለማምጣት ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል። ከከፍተኛ አመራር እስከ ቀበሌ ድረስ የሚዘልቅ አቅም፣ልምድና አመለካከትና ያማከለ የአመራር ለውጥና ሽግሽግ እንደሚደረግም አቶ ኦርዲን ገልጸዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ መሐመድ አብዱረሃማን በአሁኑ ወቅት በክልሉ በቡድተኝነትና ጎራ ተለይተው የሚከናወኑ ሕገ ወጥ ተግባራት ችግሮች እየፈጠሩ በመሆናቸው አመራሩ ከዚህ ዓይነት ተግባራት ራሱን በማራቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበዋል። ሥርዓት አልበኝነት ለመከላከልና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ክልሉን የሚመሩት የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ አቋም በመያዝ በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ መግባት አለባቸው ያሉት አቶ ያህያ ዘካሪያ ናቸው። የወረዳዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማሻሻል በአቅምና በሰው ኃይል ማደራጀትና ማጠናከር ይገባል ያሉት ወይዘሮ ሰሚራ ሐጂ ዩሱፍ ናቸው። የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገቢሳ ተስፋዬ አመራሩ በክልሉ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ተግቶ መሥራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።የሕግ ጥሰቶች ለማረምም መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ጥቅምት 29 ቀን 2011 ባካሄደው ጉባዔ የቀድሞውን የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙራድ አብዱልሃዲን በአቶ ኦርዲን በድሪ መተካቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም