በግንባታ ዘርፍ ያለው የቅድመ ዝግጅት ማነስ ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑ ተገለጸ

79
አዲስ አበባ ህዳር 3/2011 በግንባታው ዘርፍ ያለው የቅድመ ዝግጅት ማነስ ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑ ተገለጸ። የኮንስትራክሽን ሴክተር ትራንስፓረንሲ ኢኒሺዬቲቭ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንባታ ላይ ያተኮረ የጥናት ውጤት ዛሬ ይፋ አድርጓል። ኢኒሺዬቲቩ በውስጡ የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትን ያካተተ ነው። የኮንስትራክሽን ሴክተር ትራንስፓረንሲ ኢኒሺዬቲቭ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ያለው በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ የቅድመ ዝግጅት ችግር በስፋት እንደሚታይ ገልጸዋል። በአብዛኛው ግንባታዎች ከመጀመራቸው በፊት ኢኮኖሚያዊ አዋጪነት ጥናት አለመደረግ፣ የግንባታ ዲዛይን በተደጋጋሚ ጊዜ መለዋወጥ፣ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖ ግምገማ በበቂ ሁኔታ አለማካሄድ፣ ለግንባታው የሚያስፈልገውን የሰው ሃይልና ሌሎች ሀብቶች በውል አለማወቅ በግንባታው ዘርፍ በስፋት የሚታዩ ችግሮች ናቸው ብለዋል። በተለይ የኢኮኖሚያዊ አዋጪነት ጥናቶች አለመደረጋቸው ግንባታዎች መጀመሪያ ከሚያስፈልጋቸው ወጪ በላይ በግንባታው ወቅት እንዲያወጡ በማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲባክንና ግንባታው ለስርቆትና አግባብ ላልሆነ አስተዳደር የተጋለጠ እንዲሆን ማድረጉን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ጊዜ የማያልቁትና ከህዝብ የሚሰበሰብ የታክስ ገንዘብ ያለ አግባብ እንዲባክን የሚያደርገው እንዲሁም ፕሮጀክቶቹ የሚሽመደመዱት የቅድመ ዝግጅት ላይ በሚሰሩ ደካማ ስራዎች እንደሆነ ጠቅሰዋል። በቅድመ ዝግጅት ማነስ የሚታዩ ክፍተቶች ተቋራጮች የማይገባቸውን ገንዘብ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል። በቅድመ ዝግጅት ማነስ ምክንያት መንግስት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለይቶ የመስራት ስራ ላይ ችግር እየፈጠረበት እንደሆነም ነው አቶ ተስፋዬ ያስረዱት። በአጠቃላይ በግንባታው ዘርፍ ያለው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማነስ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚው ረገድ ብዙ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑንና መንግስት ጉዳዩን በከፍተኛ አጽንኦት እንዲያየው ጠይቀዋል። ግንባታውን አስመልክቶ የሚወጡ ጨረታዎች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ቢኖርም አብዛኛው የህግ ማዕቀፍ በጨረታ ሂደት ላይ የሚያተኩር እንጂ ግልጽነትና ተጠያቂነት ላይ ያተኮረ እንዳልሆነም አስረድተዋል። የግንባታ ኮንትራት አስተዳደርና ተፈጻሚነት ላይ ግልጽ የሆነ መረጃ ለህብረተሰቡ እንደማይቀርብና የኮንትራት አስተዳደሩ ግልጽ አለመሆን ሴክተሩን ለሙስና በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያጋልጠው ተናግረዋል። ላለፉት ዘጠኝ ወራት በዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በጀት ባላቸው ፕሮጀክቶች ላይ በተደረገ ጥናት በከፍተኛ ሁኔታ የግንባታ ጊዜ መጓተትና አግባብ ያልሆኑ ወጪዎች እያወጡ እንደሆነ ለማወቅ መቻሉን ጠቁመዋል። በተለይ የግንባታ ጊዜዎች ከተባለላቸው ጊዜ በአማካይ ከሁለት ዓመት በላይ ጊዜ እንደሚፈጅና በወጪ ደረጃም በአማካይ ለግንባታዎቹ የሚወጣው ወጪ ከመነሻው የ25 በመቶ በተጨማሪ ገንዘብ እንደሚወጣባቸው ጠቅሰዋል። የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ችግሩ በዋንኛነት የሚገኝበት የትምህርት ተቋም እንደሆነ ጠቅሰዋል። ደብረታቦር፣ አክሱም፣ አሶሳ፣ ሃዋሳና ወሎ ዩኒቨርሲቲ በጥናት ውስጥ ከተካተቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ይገኙበታል። አጠቃላይ ባለሙያዎች በዩኒቨርሲቲዎቹ መረጃ ለማሰባሰብ በሚጠየቁበት ወቅት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ጥናቱ በአጠቃላይ ማግኘት ካሉበት መረጃዎች 68 በመቶውን ብቻ እንዳገኘ አመልክተዋል። ጥናቱን በሶስት ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ቢያዝም መረጃ ለመስጠት ያለው የፈቃደኝነት ማነስና መረጃ ለመስጠት የነበረው ትግል ጥናቱ ዘጠኝ ወር እንዲቆይ እንዳደረውም ጠቁመዋል። በጎደለው መረጃ ምክንያት በጥናቱ የተፈለገውን ሙሉ ምስል ማሳየት ባይቻልም በአጠቃላይ ዋና ዋና የሚባሉ ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣት መቻሉን አንስተዋል። የግንባታዎች መጓተት፣ አግባብ ያልሆነ ወጪ የኮንትራት አስተደደር ግልጸኝነትና መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆን፣ የሰነድ አያያዝ ደካማ መሆንና የቅድመ ዝግጅት ማነስ በዩኒቨርሲቲው በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ላይ የታዩ ተግዳሮቶች መሆናቸው ተናግረዋል። ጥናቱ በመጀመሪያ በዩኒቨርሲቲ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳልፈለገና በአጠቃላይ በሌሎች ግንባታዎችም ላይ ማተኮር ፈልጎ እንደነበር ጠቅሰዋል። በ32 ዩኒቨርሲቲዎችና በዘጠኝ የመንግስት ተቋማት ላይ የነበረ ቢሆንም ከ41ዱ ተቋማት ዘጠኙ የመንግስት ተቋማትን ጨምሮ 27 ተቋማት በግንባታዎቻቸው ላይ ያላቸውን መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል። የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንንና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መረጃቸውን ካልሰጡ ተቋማት ውስጥ ይጠቀሳሉ። አሁንም ከ14 ዩኒቨርሲቲዎች አምስቱ ዩኒቨርሲቲዎች መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በዘጠኝ ዩኒቨርሲቲ ላይ ብቻ ጥናቱ መመርኮዙን አመልክተዋል። ''በግንባታው ዘርፍ ያሉ ተቋማት የግንባታ ፕሮጀክቶቻቸውን አስመልክቶ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ እንደማይሆኑና ፍቃደኛ የሆኑ ተቋማትም ሙሉ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደሉም'' ብለዋል። ግንባታዎች የደረሱበት አጠቃላይ ደረጃ ለህብረተሰቡ ግልጽ የሆነ መረጃ ሊቀርብ እንደሚገባና ህብረተሰቡም ይህን ሊጠይቅ እንደሚገባም ነው አቶ ተስፋዬ ያብራሩት። በአጠቃላይ በመንግስት በጀት በሚሰሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ግልጽነትና ማህበራዊ ተጠያቂነት ሊሰፍን እንደሚገባ አመልክተዋል። ኢኒሺዬቲቩ ከዚህ በፊት በጤናና ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ በመንገድና በውሃ ፕሮጀክቶች ላይ ባደረጋቸው ጥናቶች ከፍተኛ የጊዜ መጓተትና አግባብ ያልሆነ የገንዘብ ወጪ እንደሚወጣባቸውና ችግሩ በስፋት የሚታይባቸው መስኮች እንደሆኑ አመልክተዋል። በቀጣይ ኢኒሺዬቲቩ በመንግስት ህንጻዎች፣ በስታዲየሞችና በኤርፖርቶች ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። መንግስት የሚደረጉ ጥናቶችን በግብአትነት በመውሰድ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ገልጸዋል። የኮንስትራክሽን ሴክተር ትራንስፓረንሲ ኢኒሺዬቲቭ በአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያና ሰሜን አሜሪካ አህጉራት ውስጥ በሚገኙ 13 አገሮች እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ዋንኛ አላማው በህዝብ መሰረተ ልማቶች ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን መስራት ነው። ኢኒሺዬቲቩ በግንባታው ዘርፍ በጓቲማላ፣ በዩጋንዳ፣ በኤል ሳልቫዶርና በአፍጋኒስታን መሰል ሪፖርቶችን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይፋ ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም