በኦሮሚያ ክልል በሕዝብ ተሳትፎ በሁለት ሚሊዮን ሄክታር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ይከናወናሉ

70
አዳማ ህዳር 3/2011 የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ዘንድሮ ዎችንበሕዝብ ተሳትፎ ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ  እንደሚያከናውን ገለጸ ። በክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ለኢዜአ እንደገለጹት በዚህ ዓመት የሚካሄዱት ተግባራት 11 ሚሊዮን ሕዝብ ባሳተፈ ሳይንሳዊ አሰራርን በተከተለ፣በግብርና ልማትና እድገት ላይ መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ይተገበራል። በክልሉ 20 ዞኖችና 286 ወረዳዎች ላይ በሚከናወኑት ሥራዎች ከአምስት ሺህ ተፋሰሶች ለማልማትና ከ130 ሺህ ሄክታር በላይ የተጎዳ መሬት ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነፃ ይደረግበታል ብለዋል። የጥምር ግብርና በተለይም ለእንስሳት መኖና ለምግብነት የሚውሉ ሣር፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንደሚተከል ገልጸዋል። እንዲሁም አራት ቢሊዮን የተለያዩ ዝርያዎች ያላቸው ችግኞች በግለሰቦችና በመንግሥት ችግኝ ጣቢያዎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በዚህም የአፈር ለምነትን የሚያሳድጉና አሲዳማነት የሚቀንሱ ተግባራት በዘላቂነት ለማከናወንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራም  አስታውቀዋል። ባለፉት ዓመታት በሕዝብ ተሳትፎ በተከናወኑ ሥራዎች ለግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት አስተዋፅኦ ከማድረጉም ባሻገር፣የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ድርቅና ጎርፍን ለመቋቋም እንደተቻለም አመልክተዋል። ሥራዎቹን የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መድረክ ሆኖ እንዲያገለግል ጥረቱ ይጠናከራል ብለዋል ። የዘርፉን አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የፈፃሚዎችን አቅምና ክህሎት የማሳደግና ግንዛቤያቸውን ለመጨመር መሰራቱን አስረድተዋል። ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በተከናወኑ ሥራዎች የግብርናውን ዕድገት በዘላቂነት ከማሳደግ ባሻገር፤ የክልሉን የደን ሽፋን ከ15 በመቶ ወደ 23 በመቶ ማደጉን የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ናቸው። ዘንድሮ በሚካሄዱት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች አዳዲስ አሰራሮች እንደሚተገበሩበትም አመልክተዋል። በዋናነት በተራሮች ላይ ሳይንሳዊ አሰራርን መሠረት ባደረገ መልኩ የጠረጴዛ እርከን ማበጀትና የጥምር ግብርና ሥራን በመተግበር አማራጭ የሥራ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል። በኦሮሚያ ክልል  በሕዝብ ተሳትፎ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች የሚከናወኑት ለስምንተኛ ጊዜ ነው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም