ወንጀል በመፈጸም የሚገኘውን ገንዘብ ለመከላከል ዓለም ዓቀፍ መስፈርቱን ያሟላ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ መተግበር ይገባል

465

አዲስ አበባ ህዳር 3/2011 በኢትዮጵያ ወንጀል በመፈጸም የሚገኘውን የገንዘብ ዝውውር (Money Laundering) ለመከላከል የፋይናንስ ተቋማት ዓለም ዓቀፍ መስፈርቱን ያሟላ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ  መተግበር እንዳለባቸው የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ገለጸ።

ቦርዱ ከፋይናንስ  ደህንነት መረጃ ማዕከል ጋር በመተባበር ወንጀል በመፈጸም የሚገኘውን ገንዘብ መከላከል ላይ ያተኮረ ስልጠና ለባለድርሻ አካላት እየሰጠ ነው።

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋሼ የማነ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ወንጀሎች በርካታ ገንዘብ እየተሰበሰብ ለህገ ወጥ ተግባር ሲውል ይስተዋላል።

መንግስት ለፋይናንስ ዘርፉ ትኩረት አለመስጠትና በዘርፉ በቂ  ባለሙያዎች አለመኖር ገንዘብን መሰረት ያደረጉ ወንጀሎች እንዲበራከቱ በር ከፍቷል ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 847/2006 የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ዓለም አቀፍ መስፈርቱን ያሟላ እንዲሆን ድንጋጌ ማውጣቱ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብን በመተግበር ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር እንዲኖር መንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ግልጽ አሰራርና የቁጥጥር ስርዓትን ያሰፈነ በመሆኑ የፋይናንስ ተቋማትን የገንዘብ ምንጭ፣ እንቅስቃሴና ህጋዊነት በአግባቡ መቆጣጠር ያስችላል ብለዋል።

በመሆኑም የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈጸም የሚገኘውን ገንዘብ ለመከላከል የፋይናንስ ተቋማት ሪፖርት አቀራረባቸውን ዓለም ዓቀፍ መስፈርቱን ያሟላ ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

በፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል የፋይናንስ ግብይት ፍተሻና ትንተና ተጠባባቂ ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ተስፋይ ገብረእግዚአብሔር በኢትዮጵያ ገንዘብ ለማግኘት የሚፈጸሙ ወንጀሎች ብዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከነዚህም ሙስና፣ ግብር መሰወር፣ ውንብድና ወይም ማጭበርበር፣ ህገ ወጥ ሀዋላ፣ ኮንትሮባንድና ጥቁር ገበያ እንዲሁም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት ያላቸው መሆናቸው በጥናት ተለይተዋል ብለዋል።

የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል ከተመሰረተ ከስድስት ዓመት በላይ እንዳልሆነና ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ እስካሁን ከዚህ ግባ የሚባል የመከላከል ስራ አለመስራታቸውንም ገልጸዋል።

ከአሁን በፊት በማዕከሉ የህግ አገልግሎት ተብሎ ስራውን የሚያከናውነው አንድ ሰው ብቻ እንደነበር የገለጹት ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት የህግ ፖሊሲና አለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ የሰው ሃይል ተሟልቶለታል ብለዋል።

ገንዘብ ለማግኘት የሚፈጸመው ወንጀል ከተራ እስከ ዓለም አቀፍ ስለሆነ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የወንጀል ገንዘብ ዝውውር ቡድን አባል መሆናቸውንና ከተለያዩ አገራት ጋርም የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውንም ገልጸዋል።