በትግራይ 2ሺህ 206 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ሊፈቱ ነው

123
መቀሌ ግንቦት 15/2010 በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በዓመት ሁለት ጊዜ ለእስረኞች ይደረግ የነበረው ይቅርታ እንዲሻሻል መወሰኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ። የክልሉ መንግስት 2ሺህ 206 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱም ዛሬ ወስኗል፡፡ የክልሉ ፍትህ ቢሮ  ኃለፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ እንደገለጹት እስከዛሬ ባለው አሰራር የክልሉ መንግስት መስከረም መጀመሪያና ሰኔ ወር አጋማሽ በፍርድ ቤት የተፈረደባቸውን እስረኞች በይቅርታ ይለቅ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የክልሉ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ በወሰነው መሰረት በዓመት ሁለት ጊዜ ለእስረኞች ይደረግ የነበረው ይቅርታ እንዲሻሻል መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡ በእዚህም የእስረኞች ስነ ምግባር መሻሻሉ ከተረጋገጠ፣ ለፈጸሙት ድርጊት የተጸጸቱና በማረሚያ ቆይታቸው ለውጥ ያመጡ እስረኞች የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ሳይጠብቁ በማንኛውም ጊዜ በይቅርታ እንዲፈቱ የክልሉ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መወሰኑን አቶ አማኑኤል አስረድተዋል። በይቅርታ የሚለቀቁ ታራሚዎችም በፍርድ ቤቶች ከተፈረደባቸው የእስራት ቅጣት ጊዜ አንድ ሦስተኛውን ያጠናቀቁ፣ በይግባኝ ሂደት ውስጥ የሌሉ፣ ዘር በማጥፋት ወንጀል ያልተፈረደባቸው መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ በሰዎች ላይ አሰቃቂ ድብደባ በመፈጸም፣ በአስገድዶ መድፈርና በሙስና ወንጀል የተፈረደባቸው ፍርድኞች በይቅርታው ከሚፈቱት ውስጥ እንደማይካተቱ የቢሮ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የይቅርታ መስፈርቱን ያሟሉና 54 ሴት ታራሚዎች የሚገኙባቸው 2ሺህ 206 ታራሚዎች በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች እስከ ግንቦት ሀያ ባሉ ጊዜያት በይቅርታ ተፈተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደሚቀላቀሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም