የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀበለ

121
ጋምቤላ ህዳር 2/2011 የጋምቤላ ከተማና ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ያደረገላቸው አቀባበል አብሮነታቸውን በማጠናከርም ሊቀጥል እንደሚገባ ወላጆችና ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተያዘው የትምህርት ዘመን የተመደቡለትን ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሏል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ወላጆችና ተማሪዎች እንደተናገሩት ማህብረሰቡ ያደረገላቸውን አቀባበል በመማር ማስተማሩ ሂደትና  በዩኒቨርሲቲ በሚኖራቸው ቆይታ ድጋፍ በመስጠት ሊጠናከር ይገባዋል፡፡ ልጃቸውን ለማድረስ ወደ ዩኒቨርሲቲው ከመጡት ወላጆች መካከል አቶ ተሾመ ደሳሳ በሰጡት አስተያየት ለተማሪዎቹ የተደረገው አቀባበል ከጠበቅኩት በላይ አግኝቼዋለሁ ብለዋል፡፡ በአቀባበሉ ላይ የታየው አብሮነት በቀጣይም ተማሪዎቹ የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩ ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ ማንኛውም ወላጅ ልጆቹን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚልከው ከተቋሙ በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ አደራ በመስጠት ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ወላጅ አቶ ሂርጳ ደጉ ናቸው፡፡ በመሆኑም ኅብረተሰቡ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት  ሰላማዊ እንዲሆን ድርሻቸውን እንደሚወጡ እምነት አለኝ ብለዋል፡፡ ተማሪ ጫላ ቶላ በሰጠው አስተያየት በዩኒቨርሲቲው በተደረገለት አቀባበል  መደሰቱን ገልጾ፣ በቀጣይም የመጣበትን ዓላማ ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት ማህበረሰቡ ከጎኑ እንዲሆን ጠይቋል፡፡ ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ኒያል ኮት በሰጡት አስተያየት ወላጆች ልጆቻቸውን ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር ለአካባቢው ኅብረተሰብ መስጠታቸው ተገቢ መሆኑን አመልክተው፣ አደራውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ይህንንም ለማሳካት በተለይም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ተማሪዎች ከመምጣታቸው በፊት ከዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር ከተማ ጥላሁን እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የትምህርትና የምርምር ሥራዎቹን ሰላማዊና ስኬታማ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ብቃት ያላቸው ዜጎች ሆነው እንዲወጡና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለተማሪዎቹ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው አዲስ የተቀበላቸውን አንድ ሺህ አምስት መቶ ተማሪዎችን ጨምሮ ከሦስት ሺህ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎች በመደበኛ መርሐ ግብር ተቀብሎ እያሰለጠነ ነው፡፡ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው በ2007 ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም