በዳንሻ ከተማ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተመረቀ

92
ሁመራ ህዳር 2/2011 በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ዳንሻ ከተማ ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የመሰናዶ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመረቀ። የመሰናዶ ትምህርት ቤቱን ያስገነቡት የትግራይ ልማት ማህበር(ትልማ)ና ጌልፈንድ ፋሚሊ ከተባለ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው። ትምህርት ቤቱን የመረቁት በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ርስቁ አለማውና የማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ታደለ ሐጎስ ናቸው ። የትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ የቤተ ንባብ፣ የቤተ ሙከራ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የአስተዳደር ክፍሎችን ያካተተ 31 ክፍሎች እንዳለው የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ገብረየሱስ ወልዳይ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ገልጸዋል። ትምህርት ቤቱ በዳንሻና አካባቢው ከሚገኙ 18 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የ10ኛ ክፍል ትምሀርትን ያጠናቀቁ ተማሪዎችን በመቀበል እንደሚያስተምር ርዕሰ መምህሩ ተናግረዋል። በያዝነው የትምህርት ዘመን በአንድ ፈረቃ ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎችን እንደሚጀምር ተናግረዋል። ከአሁን በፊት በከተማዋ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ 105 ኪሎ ሜትር ተጉዘው በሁመራ ከተማ ቤት ተከራይተው ለመማር ይገደዱ እንደነበር ርዕሰ መምህሩ ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱ አገልግሎት በመጀመሩ የ11ኛ ክፍል ወደ ሁመራ ከተማ 105 ኪሎ ሜትር ለመማር ተጉዛ ከሚደርስባት እንግልት መዳኗን የተናገረችው የከተማው ነዋሪና የ11ኛ ክፍል ተማሪ መብርሒት አብርሃ ናት።’ በምረቃው ሥነ ሥርአት ላይ የተገኙት ዶክተር አብርሃም ተከስተ ትምህርት ቤቱ በቴክኖሎጂ የዳበረ ትውልድ ለመገንባት ያስችላል ብለዋል። በተለይም የአካባቢው ማህበረሰብ በትምህርትና በቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሴቶችን መሠረት አድርጎ መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል። በክልሉ ምዕራባዊ ዞን 65 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ42ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚገኙ ከዞኑ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም