በዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ላይ ብሔሮች ከራሳቸው በተጨማሪ የአንድ ሌላ ብሔር የባህላዊ አለባበስና የጭፈራ ትርዒት ያሳያሉ

844

አዲስ አበባ ህዳር 2/2011 ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ላይ ብሔሮች ከራሳቸው በተጨማሪ የአንድ ሌላ ብሔር ባህላዊ አለባበስና ጭፈራ ትርዒት እንደሚያሳዩ ተጠቆመ፡፡

የ13ኛው የኢትዮጵየ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዝግጅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ፣ የክልሎች ምክር ቤቶች አፈ-ጉባዔዎች የበዓሉ አስተባባሪ ጽህፈት ቤትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ በአዲስ አበባ ተገምግሟል።

የበዓል ዝግጅት አስተባባሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኑረዲን ማህሙድ እንዳሉት፤ በዓሉ አገራዊ አንድነት፣ ሰላምና መቀራረብ ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ከነዚህም መካከል የራስ ብቻ ሳይሆን አንዱ ብሔር የሌላውንም ባህል ጨምሮ እንዲያሳይ ለማድረግ ሁሉም የቤት ስራ ወስዶ ዝግጅት እንዲጀምር መደረጉ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት ትግራይ ክልል ከራሱ በተጨማሪ የኦሮሞ ህዝብን ባህል የሚያሳይ ትዕይንት ለማሳየት፣ ኦሮሚያ ክልል ደግሞ ከደቡብ ብሔሮች መካከል የተወሰኑትን መርጦ፣ ደቡብ ደግሞ የአማራን አማራ ደግሞ የሱማሌን ለማሳየት ፍቃደኛ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ሁሉም ክልል ከራሱ በተጨማሪ የሌላውን ክልል አንድ ወይም ከዚያ በላይ ብሄር ባህላዊ አለባበስ ጭፈራና ትዕይንቶችን ለማሳይት ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ በዓሉ ሲከበር አገራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ ምክክሮች በማድረግ እንዲሆንና ሲምፖዚዬሞች እንዲዘጋጁ በመወሰኑ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሁፎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች በተለይ ደግሞ ግጭቶች ተከስተው በነበሩባቸው አካባቢዎች ላይ ሁሉም የሚሳተፍበት ህዝባዊ መድረክ በማዘጋጀት ውይይትና እርቅ እየተደረገ እንደሆነ አመላክተዋል።

ከዚህም ሌላ ለትውውቅ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ኢንተርፕራይዞች ትስስር የሚፈጥሩበት ባዛርና ኢግዚቢሽን ተዘጋጅቶ 10 ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

”ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ” የሚል መርሃ ግብር በበዓሉ አስተናጋጅ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማካኝነት እንደሚዘጋጅም አቶ ኑረዲን ጠቁመዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ የክልሎች ምክር ቤቶች አፈ-ጉባዔዎች እንዳሉት፤ ተመሳሳይ ፕሮግራሞችና የውይይት መድረኮች በማዘጋጀት ላይ እንደሆኑና በአዲስ አበባ የሚከበረው ዋናው በዓል ላይ አገራዊ አንድነት የሚያጎላ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው እየተዘጋጁ ነው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው በዓሉ ሲከበር ዋናው ትኩረት አገራዊ ትስስር ማጠናከርና የነበረውን የአብሮነት እሴት ማዳበር ላይ መሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለዚህ ደግሞ የአንድ ህዝብ ወይም ብሔር ባህል የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ባህል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ያሉት አፈ-ጉባዔዋ ከዚህ በፊት እንደነበረው የራስን ባህላዊ አለባበስና ጭፈራ ማሳየት ላይ የማተኮር አስተሳሰብ ሊቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም አንዱ ብሔር ከራሱ በተጨማሪ የሌላውን ባህል ማሳየትና ማስተዋወቅ ለትውልድ በጎ ነገር እንደሚያስተመርም ገልጸዋል።

ግጭቶች የነበሩባቸው አካባቢዎች ላይ ወደ ህዝብ ወረድ ብሎ በማወያየትና እርቅ እንዲወርድ መስራት ትኩረት የሚሰጠው እንደሆነም አብራርተዋል።

በዓሉ ዘንድሮ ”በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ይከበራል።