አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መስተዳድር ሆኑ

74
ጋምቤላ ህዳር 2/2011 የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ትናንት ማምሻውን ባካሄደው አራተኛ የሥራ ዘመን ሦስተኛ አስቸኳይ ጉባኤ አቶ ኡሞድ ኡጁሉን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክን ደግሞ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾመ፡፡ ምክር ቤቱ አዲስ ዋናና ምክትል ሹመቱን የሰጠው የቀድሞው ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱትና ምክትላቸው አቶ ሰናይ አኩዎር ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ በምክር ቤቱ ተቀባይነት በማግኘቱ ነው፡፡ አቶ ጋትሉዋክ ቱት የስለጣን መልቀቂያ ጥያቂያቸውን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት ፈተናዎችን በመቋቋም በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሀብትና ፖለቲካዊ ዘርፎች በርካታ ለውጦች ለውጦች ተመዝግቧል። ይሁን እንጂ ከአገራዊ እድገት ጋር ተያይዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የክልሉን ህዝብ የልማት ፍላጎት የሚመጥን ምላሽ አለመስጠቱን ተናግረዋል፡፡ “በህዝቦች የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የክልሉ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ወቅታዊ ምላሻ ባለማግኘቱ ብሶቱን ወደ አደባባይ ለመውጣት ተገዷል” ብለዋል፡፡ ክፍተቶቹን ለመሙላትና የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የሚችሉ ጠንካራ ወጣት አመራሮች መተካት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን ከርዕሰ-መስተዳድርነት ሥልጣን ቢነሱም፤ ካለፉት ስህተቶች በመማር በቀጣይ በማንኛውም የሥራ መስክ የለውጡ አካል በመሆን የክልሉን ህዝብ ለመካስ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። አቶ ኡሞድ ባደረጉት ንግግር በበኩላቸው በክልሉ ለነበረው የሥልጣን ሽኩቻ፣ የዘረኝነትና የጎሰኝነት አመለካከት ምክንያቶቹ በክልሉ ከአጠቃላይ አገራዊ እድገቱ ጋር የሚጣጣም እድገት ሳይመጣ መቆየቱ ገልጸዋል። ለህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና በክልሉ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። ወጣቱን የለውጡ አካል በማድረግ በተለይም ብሔርተኝነትን፣ ጎሰኝነትንና ሙስናን በመታገል በአገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ ወደፊት ማራመድና የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የዋነኛ ትኩረታቸው እንደሚሆን  አመልክተዋል።                የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር ማድረግም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር ገልጸዋል። የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ላክድር ላክባክ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ለውጡን በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም አመራር በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል። “ምክር ቤቱ የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ከማድረግ ባለፈ በአስፈጻሚ አካላት ላይ የተጠናከረ ክትትል በማድረግ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ውጤታማ  እንዲሆኑ ጭምር ይሰራል” ብለዋል፡፡ ጉባዔው አዲሶቹን ዋናና ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሮች የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እንዲሆኑም ወስኗል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም