የቀብሪ ደሃር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ አሟሙቀውታል

76
ጅግጅጋ  ህዳር 2/2011 የቀብሪ ደሃር ዩኒቨርሲቲ ነባር ተማሪዎች መግባታቸውን ተከትሎ የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ መነቃቃት ማሳየቱን ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡ ተማሪዎቹ በግልና በጋራ በመሆን ከሚገዟቸው መካከል የሶማሌ ሴቶችና ወንዶች ባህላዊ አልባሳትና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ይገኙባቸዋል፡፡ አቶ አብዲ ኑር 02 ቀበሌ የተዘጋጁ የልብስ መሸጫ መደብር ባለቤት ናቸው።ተማሪዎቹ ገበያው ዕቃዎች በሚገዙ ተማሪዎች ደምቋል ይላሉ፡፡ የከተማው የንግድ እንቅስቃሴ ተማሪዎቹና መምህራኑ ለዕረፍት በቆዩባቸው ወራት ተቀዛቅዞ እንደነበር ያስታውሳሉ። ተማሪዎቹ በመምጣታቸው ቤት አከራዮች፣ ምግብ ቤቶች፣ የልብስና ሸቀጣሸቀጥ መደብሮች እንቅስቃሴ መነቃቃት ማሳየታቸውን አቶ አብዲ ገልጸዋል፡፡ የቀብሪደሃር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዲራህማን መሐመድ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከነዋሪዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥብቅ መሆኑንና ግብይትም የዚሁ ግንኙነት አንዱ መገለጫ መሆኑን አስታውቀዋል። በከተማዋ ባለፉት አራት ዓመታት የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ግንባታ በስፋት እየተከናወነባት መሆኑን አስታውቀዋል። ዩኒቨርሲቲው ለ400 ነዋሪዎች ቋሚ ሥራ መፍጠሩም ሌላው የከተማዋ ትሩፋት ነው ብለዋል። ከጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን የመጣችው ተማሪ አኬሎ ኡመድ ''የልብስና የመኝታ አልባሳት ዋጋ ተመጣጣኝ በመሆኑ በተማሪ አቅም መግዛት አይከብድም'።የማህበረሰቡን ባህል ለማህበር የሶማሌ ሴቶች ልብስ ገዝቻለሁ'' ብላለች፡፡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ከተማው ስትመላለስ የአካባቢውን ህዝብ የባህል ልብስ ለብሳ መታየት የተለየ ደስታ እንደሚሰጣትም ገልጻለች፡፡ ተማሪ ትዕግሥቱ ዓለሙ ከአካባቢው ሙቀት ጋር የሚስማማ  የአልጋ ልብስ በተመጣጣኝ ዋጋ መፈጸሙን ተናግሯል።ኅብረተሰቡ እያደረገላቸው አቀባበል አስደሳች ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል። የቀብሪ ደሃር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አብዲፈታህ አህመድ ዩኒቨርሲቲው ከማህበረሰቡ ጋር ከ400 በላይ ነባር ተማሪዎች መቀበሉን አስረድተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአራት ኮሌጆች እና በ15 ትምህርት ክፍሎች 1ሺህ 500 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በሶማሌ ክልል የሚገኘው የቀብረ ደሃር ዩኒቨርሲቲ ሥራ የጀመረው በ2010 ነበር።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም