በዘላቂነት እንድንቋቋም የተፋጠነ ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል---በድሬዳዋ በመጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች

50
ድሬዳዋ ህዳር 1/2011 ህይወታቸውን በዘላቂነት መምራት እንዲችሉ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው በድሬዳዋ ከተማ በመጠለያ የሚገኙ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ተፈናቃዮች ጠየቁ። ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን የድሬዳዋ ከተማ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት ከሁለቱም አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከዘጠኝ ሺ በላይ ዜጎች ድሬዳዋ ተጠልለው መቆየታቸው ይታወሳል። በአሁን ሰዓት ካለፈው ዓመት መስከረም ጀምሮ በድሬዳዋ ሁለት መጠለያዎች ከ4240 በላይ የሶማሌ ክልል ተወላጆች የሚገኙ ሲሆን ነዋሪዎች ከተረጂነት ተላቀው ዘላቂ ህይወታቸውን የሚመሩበትን እለት እየጠበቁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል። በመጠለያው የሚኖሩት ወይዘሮ አይሻ ሐሰን “መንግስት ፣ ህብረተሰቡ ሌሎችም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በምግብ ፣በልብስ፣ በህክምና በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጭምር ድጋፍ እያደረጉልን ነው፤ እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡ በአንድ ስፍራ ተጨናንቀው ከአንድ ዓመት በላይ አሰልቺ ህይወትን እየመሩ መሆናቸውን ገልጸው ለዚህም ዘላቂ ሊሰጥበት እንደሚገባ አመልክተዋል። “ድንገት ወረርሽኝ ቢከሰት ሊፈጠር የሚችለው ጉዳት መገመት አይከብድም” ያሉት ደግሞ ሌላው ቅሬታ  አቅራቢ አቶ ከሊፍ ሪያሌ ናቸወ፡፡ በድሬዳዋ ሙቀት በፕላስቲክ ጎጆ መኖር ከባድ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማስፈር የጀመረውን ጥረት በፍጥነት ማጠናቀቅ እንዳለበት ጠይቀዋል። ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመጓዝ  ዝግጅቱን ያጠናቀቀው ተማሪ ሙስጠፋ አሊ በበኩሉ በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግኖ በህይወት የሚገጥማቸውን ችግር ተቋቁመው ነገ የተሻለ ስፍራ ለመድረስ በትምህርቱ መበርታቱን ተናግሯል፡፡ “ልጆች ከመጠለያ እስኪወጡ ድረስ ባሉበት ቦታ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ መልካም ይመስለኛል” ብሏል፡፡ የድሬዳዋ አደጋ ስጋት አመራር ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ እንደገለጹት  4ሺህ200 አባላት ላላቸው 1ሺህ 400 ቤተሰቦች በፌዴራል መንግስት፣በሶማሌ ክልል፣በከተማ አስተዳደሩና በግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ትብብር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተሰራ ነው። በቅርቡ ከሶማሌ ክልል አመራሮች ጋር በተደረገ ውይይትም በመጠለያ የሚገኙ ትክክለኛ ተጎጂዎችን በመለየት ክልሉ ከ4 እስከ 6 ወራት በሚሆን ጊዜ በቋሚነት የማስፈር ሥራ  መጀመሩን ተናግረዋል። በእስከ አሁን በከተማ አስተዳደር ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣቱን ጠቁመው “ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚጓዙት ተማሪዎች የትራንስፖርትና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል” ብለዋል፡፡ በድሬዳዋ ሀምሌ 29 ቀን 2010 ገንደ ገራዳና ለገሀሬ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ከ1ሺ450 በላይ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው የመመለሱ ሥራ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንደሚከናወን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም