በፌዴራል ስርዓቱ የተመዘገቡ ለውጦችን ለማስቀጠል የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ይገባል ---ምሁራን

74
አክሱም ግንቦት 15/2010 በፌዴራል ስርዓቱ የተመዘገቡ  ለውጦችን ለማስቀጠል የአስፈጻሚ አካላት ብቃትና የዴሞክራሲ ተቋማትን ግንባታ ማጠናከር  እንደሚገባ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለተካ ሳይንስ ምሁራን አመለከቱ። በዩኒቨርሲቲው  የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ነጋ ሰለሞን ለኢዜአ እንዳሉት የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ኢትዮጵያ የተረጋጋች ሀገር ሆና እንድትቀጥልና በአለም አቀፍ መድረክ ተደማጭነቷ እንዲጨምር አድርጓል። " ለተመዘገበው ሰላም፣ልማትና እድገት መሰረቱ የፌደራሊዝም ስርዓት ነው" ያሉት ዶክተር ነጋ ፣በቀጣይም ህብረተሰቡ በሚፈልገው ደረጃ ለመተግበር መንግስት በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል። በተጨባጭ የፌደራል ስርዓቱ የፈጠራቸው ችግሮች እንደሌሉና  ችግሩን በማስፈጸም ብቃት ማነስ የሚከሰት መሆኑን አውስተዋል፡፡ "የፌዴራል ስርዓት ግንባታ ለማጠናከርና የተጀመረውን ጉዞ ለማስቀጠል በአስፈጻሚ አካላት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የአቅም ግንበታ ስራ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል። ዶክተር ነጋ እንዳመለከቱት የስርዓቱ ፈተና የሆኑት የመልካም አስተዳደር እና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን  ለማስወገድ  የፌደራሊዝም ስርዓት ምንነትን ተገንዝቦ የሚተገብር አስፈጻሚ አካል ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ሓዱሽ ረዳኢ በበኩላቸው " ባለፉት 27 ዓመታት የፌደራሊዝም ስርዓቱ በኢትዮጵያ ታሪክ አሁን ላለንበት የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት መሰረት ጥሏል " ብለዋል፡፡ አሁንም ብሔርተኝነት፣ኪራይ ሰብሳቢነት፣ትምክህትና ጠባብነት ለፈደራል ስርዓቱ ዋንኛ ስጋቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ስጋቶች ህብረተሰቡን በማሳተፍ መፍታት እንደሚቻልና በሂደትም የፌደራል ስርዓቱ  ሲጎለብት የሚፈታቸው መሆኑን ገልጸዋል። ፌደራል ስርዓቱ በሂደት ያለና ጥሩ ለውጥ እያመጣ ያለ እንደሆነ  ያመለከቱት አቶ ሓዱሽ ህገ መንግስቱና ፌደራላዊ ስርዓቱ በሚገልጸው መንገድ  ለመተግበር ጊዜ እንደሚያስፈልገውም ጠቁመዋል። የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ እንዳሉት የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል ባለፉት መንግስታት የተፈጸሙ ስህተቶችን በመውቀስ ሳይሆን በአዲስ አስተሳሰብ በሂደት ያለውን የፌደራል ስርዓቱ ማጎልበት የመንግስት ትልቅ የቤት ሰራ ነው። የፌደራል ስርዓቱ ያመጣቸውን ለውጦች በመገንዘብ  አንድነት፣ ፍቅር፣ ልማት እና ብሄራዊ መግባባትን የሚሰብኩ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል። "በፌደራል ስርዓት እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የፍትሕ አካላት፣ የመገናኛ ብዙሃን ፣ ሲቪክ ማህበራት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች በማጠናከርና በቅንጅት እንዲሰሩ በማነሳሳት  ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል "ብለዋል። ወጣቱ የሀገሪቱን ሰላም በመጠበቅ ሀገራዊ የአንድነት ስሜት ግንባታ እና የፌደራሊዝም ስርዓት ሂደቱን ለማጠናከር ማስተማር እንደሚገባም ምሁራን መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። የፖለተካል  ሳይንስ  መምህሩ ገብረመድህን መዝገበ በሰጡት አስተያየት የፌደራል ሰርዓቱ በህዝቦች መካከል ፍትሓዊ ተጠቃሚነትን እንዲረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጰያውያን መካከል ለዘመናት የቆየውን ፍቅርና  በጋራ የመኖር እሴት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡ "ብዝሃነትን  ለማስተናገድ የፈደራሊዝም ስርዓት  የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ብቸኛ አማራጭ ነው " ያሉት መምህር ገብረመድህን፣ ከነበረው ኋላቀርነትና ጦርነት በመውጣት የሀገሪቱን  ገጽታ የቀየረ መሆኑን ተናግረዋል። አድሎአዊ አሰራር፣የመልካም አስተዳደር እና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን በመፍታት የፌደራሊዝም ስርዓቱን ማስቀጠል እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም