የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪ በመቀበል ወጤታማ ለመሆን እንተጋለን---የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

63
ሆሳእና ህዳር 1/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለተማሪዎች ያስተላለፉትን ጥሪ በመቀበል በትምህርታቸው ውጤታማ ለመሆን እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን የሰጡ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የ4ኛ ዓመት የጤና ሳይንስ ኮለጅ ተማሪ ጌድዮን ተስፋዬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልእክት "ወቅቱ ቆመን የምንመለከትበት ሳይሆን ሮጠን ውጤት የምናስመዘግብበት ነው" ማለታቸውን አስታውሷል ። "ጥሪውን በመቀበል ጊዜውን  በአግባቡ በመጠቀም የመጣሁበትን ዓላማ ለማሳካት እሰራለሁ" ብሏል ። አብዛኛው ጊዜውን ለንባብ በማዋል የዘርፈ ብዙ እውቀት ባለቤት ለመሆን እንደሚተጋም ነው የገለጸው ። “ህብረ ብሔራዊነት ለእኛ ውበት በመሆኑ ውበታችንን በመጠቀም ሌሎች ሀገራትን መሳብ መቻል አለብን” ያለችው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የ2ኛ ዓመት የማኔጅመንት ተማሪ ሉሊት ስንታየው ናት፡፡ "ዩኒቨርሲቲዎች የህብረ ብሄራዊነት መገለጫዎች በመሆናቸው ተማሪዎች ቋንቋ፣ ታሪክና ባህላችንን በመለዋወጥ ኢትዮጵያዊነታችንን ማጠናከር ይገባናል" ብላለች፡፡ ተማሪዋ እንዳለችው የምትማርበት ተቋም የግጭትና አልባሌ ተግባር መፈፀሚያ እንዳይሆን የበኩሏን ትወጣለች። የሦስተኛ ዓመት የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ ጫላ ፈይሳ በበኩሉ "ተማሪዎች በመካከላችን አለመግባባት ሲፈጠር ያልተግባባንበትን ምክንያት መረዳት እንጂ ወደ ግጭት ማምራት አይጠቅመንም " ብሏል ። "የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአንድ እናት ልጆች ነን፤ የአንድ እናት ልጆች ላይግባቡ ቢችሉም ወደ ግጭት አያመሩም" ሲል ሀሳቡን አጠናክሯል። ከአደንዛዥ እጽ ራሱን በጠበቅና ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ ውጤታማ በመሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱንም ተናግሯል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ሲሳይ ዮሐንስ በበኩላቸው ተማሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚስቸሉ ዝግጅቶች በዩኒቨርሲቲው በኩል ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ተማሪዎች የንባብ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ የሚረዱ የመጻፍት አቅርቦት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ። "ችግሮች ሲያጋጥሙ በውይይት መፍታት እንደሚቻል ከአዲስና ከነባር ተማሪዎች ጋር ውይይት ተደርጓል" ብለዋል ። እንደ ተማሪ ሲሳይ ገለጻ ዘንድሮ በተማሪዎች መካከል ሕብረ ብሔራዊነትን ይበልጥ ለማጠናከር ሲባል አዲስ ተማሪዎችን በመኝታ ክፍሎች በብሔር ስብጥር እንዲደለደሉ ተደርጓል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም