በኢትዮጵያ በሳይንስ ዘርፍ የመጣው ለውጥ መነቃቃትን ፈጥሯል

79
አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 የ16 አመቱ ተማሪ ሜላን መሐመድ በኢንቴሌክችዋል ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በስፔስ ሳይንስ ዙሪያ ሁለት መፅሀፍትን አሳትሟል። በዘርፉ ያሉ መፅሀፍትን ያነብና ዘጋቢ ፊልሞችን ይመለከት እንደነበር የገለፀው ሜላን በ13 አመቱ "ዘ ስፔስ" የተሰኘ ባለ 50 ገፅ መፅሀፍ በማሳተም አማዞን ላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጿል። በሚወስዳቸው ኦን ላይን ኮርሶች ከቶኪዮና ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲዎች የምስክር ወረቀት ባለቤት መሆን ችሏል። የመጀመሪያ መፅሀፉን የፃፈው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ሲሆን በአመቱ ደግሞ "ኢንተርናሽናል ስፔስ ስቴሽን" የሚል ሁለተኛ መፅሀፉንም ፅፎ አጠናቋል። በኦን ላይን በተደረገ ውድድርም ከኤር ባስና ናሳ ምስክር ወረቀትያገኘው ሜላን እነዚህን ምስክር ወረቀቶች በማህበራዊ ድረ-ገፅ በማጋራቱ ከቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የአድናቆት ደብዳቤ በኢ-ሜይሉ እንደተላከለትም አብራርቷል። ሜላን ሁለቱን መፅሀፍት ባሳተመበት ወቅት ነዋሪነቱ ሳዑዲ አረቢያ እንደነበር ገልፆ በአገሪቱ የስፔስ ክለቦች እንዳልነበሩ ገልጿል። ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የዛሬ ዓመት መሆኑንና በኢትዮጵያ የተሻለ አደረጃጀት በመኖሩ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ አባል እንዲሁም በሚማርበት ትምህርት ቤት ስፔስ ሳይንስ ክለብ ፕሬዝዳንት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ይናገራል። ኢትዮጵያ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2019 ሳተላይት ልታመጥቅ መሆኗና በስፔስ ሳይንስ ዙሪያ የሚሰሩ ማህበራትና ክለቦች መኖራቸው ዘርፉን ለማስፋፋት ዕድል እንደሚፈጥርለት ያስረዳል። በዛሬው ዕለትም የቀድሞ የናሳ አስተዳዳሪ ቻርልስ ቦልደን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለተማሪዎች ገለፃ ማድረጋቸው ይበልጥ መነሳሳትን እንደፈጠረለት ተናግሯል። እንደ ሜላን ሁሉ ስለ ስፔስ ሳይንስ በቀድሞ የናሳ አስተዳዳሪ ቻርልስ ቦልደን የተደረገው ገለፃ በዘርፉ ያላቸውን እውቀት እንደጨመረላቸውና ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተስፋ እንዳሳያቸው ተማሪ ሲሳይ ፋንታሁን እና ሀዊ የኋላእሸት ገልጸዋል። ተማሪዎቹ የአዲስ አበባና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ ያለውን መነቃቃት የሚያሳዩና ዘርፉን ለማዘመን የሚረዱ በመሆናቸው እንዲህ አይነት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። የቀድሞ የናሳ አመራርና የአሁኑ የአሜሪካ የሳይንስ ልዑክ ቻርልስ ቦልደን በበኩላቸው ከአራት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሳይንስና ቴክኖሎጂና ወጣት ስራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ "አስገራሚ ለውጥ" መኖሩን አብራርተዋል። አገሪቱ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ሳተላይት ልታመጥቅ መሆኑ የለውጡ አንድ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቀድሞ በሳይንስ ዙሪያ የሰሩና ፍላጎት ያላቸው መሆኑ እንዲሁም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ባደረጉት ውይይት አገሪቱ በቀጣይ በዘርፉ ሰዎችን ለማብቃትና ለማዘመን ብዙ እንደምትሰራ አመላካች መሆኑን አስረድተዋል። በአሜሪካ ኤምባሲ የምስራቅ አፍሪካ የሳይንስና አየር ንብረት አስተባባሪ ክርስቶፈር ናይስ እንደተናገሩት ቻርልስ ቦልደን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ጋር በስፔስ ሳይንስ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። የዛሬው የማነቃቂያ መድረክም ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ያላቸውን ጠቀሜታ ለወጣቶች ለማስረዳትና በዘርፉ የተሰማሩና ፍላጎት ያላቸውን ይበልጥ ለማነሳሳት ነው። የቀድሞው የናሳ መሪ ቻርልስ ቦልደን ለአንድ አመት የአሜሪካ የስፔስ ሳይንስ ልዑክ ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ወደ ዮርዳኖስ አቅንተው ነበር። በቀጣይም በተመሳሳይ መልኩ ወጣቶችን ለማነቃቃት ወደ ደቡብ አፍሪካና ህንድ የሚያቀኑ ይሆናል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም