በህብረ-ብሔራዊ አንድነት የጠነከረ ሰራዊት ተገንብቷል-የመከላከያ ሰራዊት አባላት

87
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በህብረ-ብሔራዊ አንድነት የጠነከረ ሰራዊት መገንባቱን ገለጹ፡፡ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰራዊቱ አባላት እንዳሉት በሰራዊቱ ውስጥ ባለው ህብረ-ብሔራዊነት ትንሿን ኢትዮጵያ መፍጠር ተችሏል። ሻምበል እንግዳ እንዳለ ባለፉት ዓመታት ለህዝቦችና ለአገር ክብርና ሉዐላዊነት  እስከ ህይወት መስዋዕትነት የመክፈል ኃላፊነት የተሸከመ የመከላከያ ሰራዊት መገንባቱን ተናግረዋል። ሻለቃ ንጉሴ ኃይለማርያም እንዳሉት ደግሞ በህገ መንግስቱ በሰፈሩ የመከላከያ መርሆዎች መሰረት ዘመናዊ ሰራዊት መገንባት  ተችሏል። ሌተለናል ኮሎኔል መሰረት አየሁም በህብረ-ብሔራዊ አንድነት የጠነከረ ሰራዊት መመስረቱን ግልጸዋል። ሁሉም የሰራዊቱ አባላት የአመለካከት አንድነትን በመያዝና የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠል ያላቸው ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ጠንካራ መሆኑንም ነው ያብራሩት። ሻምበል ጌታቸው አብርሃ እንደገለጹት የኢፌዴሪ መከላከያ  ሰራዊት ከአገሪቱ አልፎ የሌሎች አገሮችን ሰላም በማስከበር ረገድ ተልዕኮውን በብቃት ከሚወጣበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በአገሪቱ ፈጣንና ቀልጣፋ የልማት ዕድገት ማስመዝገብ የተቻለውም ለአገሪቱ ሰላምና ዴሞክራሲ ዘብ የቆመ ህዝባዊ ሰራዊት በመፈጠሩ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ማዕከል ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል ሃብታሙ ጥላሁን  እንደገለጹት "ከ1987 ዓም በኋላ የመከላከያ ሰራዊቱን የብቃትም ሆነ የልምድ ክፍተቶች በስልጠና፣ በትምህርትና በውጊያ ብቃት በማረጋገጥ የብሄር፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ተዋፅኦ ያረጋገጠ ሰራዊት መገንባት ተችሏል።" "በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የታጠቀ፣ በወታደራዊ ዶክተሪን፣ ሳይንስና ጥበብ የተካነ ጠንካራ ሰራዊት ተመስርቷል" ነው ያሉት። ሰራዊቱ የአገሪቱን ሰላም ከማስከበር ባሻገር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ብቃቱ መረጋገጡን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አገራት 12 ሺህ 500 የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሰላም ማስከበር ተልእኮ ተሰማርተው ይገኛሉ። አገሪቱ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ከውጭ ወራሪና ከውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚጠብቅና የተሰጠውን ግዳጅ በተነሳሽነትና በላቀ ውጤት መፈጸም የሚችል የመከላከያ ሰራዊት መገንባቷም ነው ከፍተኛ መኮንኑ የገለጹት። ብርጋዴር ጀነራል ሀብታሙ እንዳሉት ከዓለም አቀፋዊ የመከላከያ ኃይል ተቋም ግንባታ ተሞክሮና ባህርይ አኳያ የአባላቱን የትግል ተሳትፎ፣ በትግሉ ወቅት ያሳዩትን ልዩ ብቃትና የትምህርት ደረጃቸውን መሰረት በማድረግ የማደራጀትና የማሰባጠር ስራ መሰራቱን ተከትሎም የሰራዊቱ የመፈጸም ብቃት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከግንቦት 20 /1983 እስከ 1987 ዓ.ም የኢህአዴግ የሽግግር መንግስት ሰራዊት የተመሰረተ ሲሆን በ1987 ዓ.ም ደግሞ  በህገ-መንግስቱ መሰረት ህብረ-ብሄራዊ ሰራዊት እንዲዋቀር ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም