የጀጎል ግንብን ከጉዳት ለመታደግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመለከተ

101
ሀረር ህዳር 1/2011 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፥ የሳይንስ እና የባህል ተቋም/ ዩኔስኮ/ በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብን ከጉዳት ለመታደግ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የአካባቢው ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡ የግንቡ  እድሳት በቅርቡ እንደሚጀመር የሐረሪ ክልል ባህል፣ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ገልጿል። በሐረር የኤረር በር ነዋሪው ወይዘሮ አሊያ አህመድ ለኢዜአ እንዳሉት  የጀጎል ግንብ በውስጡ  ታሪካዊ፣ኃይማኖታዊና ጥንታዊ  መስህቦች የሚገኝበት ስፍራ ነው፡፡ " በቱሪስቶችም ዘወትር ይጎበኛሉ፤ በአሁኑ ወቅት ግን  የግንቡ ዙርያ እየፈረሰ ይገኛል"ብለዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዋ በተለያዩ ጊዜያት የክልሉና የፌዴራል ስራ ኃላፊዎች እየመጡ ቢመለከቱትም የተሰጠው መፍትሄ ባለመኖሩ በአሁኑ ወቅት የግንቡ አካል እየደረሰበት ያለው ጉዳት በመባባሱ የክልሉ መንግስት ሊታደገው ይገባል። የመስህብ ስፍራ በመሆን በክልሉ ገቢ ከሚያስገኙት መካከል አንዱ የጀጎል ግንብ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ መምህርት ቱጡኝ ዩስፍ ናቸው፡፡ " ግንቡ መፍረስ ከጀመረ ሁለት ዓመት ሆኖታል፤ እንክብካቤ የሚያደርግለት አካል የለም" ብለዋል፡፡ ቅርሱ ለትውልድ ለማስተላለፍ ትኩረት ተሰጥቶ ጥገና  ሊደረግለት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ አቶ አዳሙ ቢኒያም የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው ታሪካዊ ቅርስ የሆነው የጀጎል ግንብ ጉዳት አሳሳቢ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መታደግ እንዳለበት ጠቁመዋል። ቀደም ሲል የክልሉ መንግስት ተከታትሎ  ጥገና ያደርግለት እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ ሌላው ነዋሪ  አቶ አብዲ አደም ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዘንጋቱ ለጉዳት መጋለጡን ጠቅሰው ታሪካዊ ቅርስ እና  የቱሪስት መስህብ እንደመሆኑ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በክልሉ ባህል፣ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ የቅርስ ዳይሬክተር አቶ ነቢል በክሪ በበኩላቸው  በአለም ቅርስነት የተመዘገበውና በበርካታ ቱሪስቶች የሚጎበኙት ታሪካዊው  የጀጎል ግንብ ከጉዳት ለመታደግ በየዓመቱ የጥገና ስራ ሲከናወን መቆየቱን  አመልክተዋል፡፡ በእርጅናና በውስጡ የሚኖሩ ነዋሪዎች በሚያደርሱበት ጉዳት በአሁኑ ወቅት በግንቡ በተለያዩ ሶስት ስፍራዎች ላይ የመፍረስ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጸዋል፡፡ እየደረሰበት ካለው ጉዳት  ለመታደግ በተያዘው በጀት ዓመት ግማሽ ሚሊየን ብር የሚጠጋ በጀት መመደቡንና በቅርቡም የጥገና ስራ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው ታሪካዊው የጀጎል ግንብ ፣ በውስጡ  ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶችና አምስቱ መግቢያ በሮች ፣ ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣  የሐረሪ  ሙዚየሞችና የእምነት ቦታዎች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም