የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

76
ሶዶ ህዳር 1/2011 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት አሳሰበ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታመነ ተሰማ ለኢዜአ እንደገለጹት እንደ ሃገር የተጀመረውን የሰላምና የለውጥ ሂደት ያልተቀበሉ ግለሰቦች ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ የህዝብ ወገን ነኝ የሚል ጥያቄ በማንገብ ሁከት ለመፍጠር የሚጥሩ አካላት ስልታቸውን በመቀየር ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መዝለቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ  ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉና ወደ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲም ዘልቆ ችግር እንዲፈጠር ለማድረግ ተሞክሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የክልሉን ሰላምና ለውጥ የማይፈልጉ ግለሰቦች በተለይም የወላይታና ሲዳማ ህዝቦችን ሽፋን በማድረግ እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም እየተጉ መሆናቸውንም መንግስት መገንዘቡን አመልክተዋል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት  አቶ ታመነ "ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የክልሉ መንግስት እየሰራ ነው "ብለዋል፡፡ በዚህም የእርስ በርስ የመከባበር ማህበራዊ እሴቶቻችንን ለማጉላት የተቀናጀ ስራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በሃዋሳና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች መካከልም ተጨባጭ ያልሆነ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን በማናፈስ የተረጋጋ የመማር ማስተማር ስራ እንዳይከናወን በተቋማቱ መካከል ምክክር እንደሚደረግም ጠቅሰዋል፡፡ "በተቋማቱ  መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር የተረጋጋና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስፈን የክልሉ መንግስት አቅዶ እየሰራ ነው" ብለዋል፡፡ ወጣቱ ባለቤት ለሌለው አሉባልታና መሰረተ ቢስ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬ  ትኩረት ከመስጠት መቆጠብ እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የክልሉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው "የክልሉን ሰላም ለማወክ ያልተሳካላቸው ኃይሎች  ወጣቱንና የትምህርት ተቋማትን አነጣጥረው እየሰሩ ነው "ብለዋል፡፡ በወላይታና ሲዳማ ህዝቦች መካከል ችግር እንዳለ ለማስመሰል ውዥንብር በመፍጠር የትምህርት ስራ ለማወክ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ችግሮችን በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ ለመፍታት ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶቻችንን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ መጠናከር መስሪያ ቤታቸው የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም