የጣና ሐይቅ የዓሣ ምርት መጠን በዓመት እስከ 2 ሺህ ቶን እየቀነሰ ነው፡- አንድ ጥናት

100
ባህር ዳር ህዳር 1/2011 የጣና ሐይቅ የዓሣ ምርት መጠን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት በዓመት እስከ 2 ሺህ ቶን እየቀነሰ መምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ። ምርቱ እየቀነሰ መምጣቱ የተረጋገጠው በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባህር ዳር ዓሣና ሌሎች የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል ባካሄደው ጥናት ነው። የምርምር ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ተዋበ ለኢዜአ እንደገለጹት በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተው የእምቦጭ አረም እና ህገ-ወጥ አስጋሪዎች የሚጠቀሙበት ኢ-ሳይንሳዊ የማስገሪያ መረብ የሐይቁ የዓሣ ምርት በፍጥነት እየቀነሰ እንዲመጣ አድርጓል። ከክልሉ አልፎ ለአገር ስጋት እየሆነ የመጣው የእምቦጪ አረም የአዓሣዎችን ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ከመግታት ባለፈ ሐይቁን በመሸፈኑ ምክንያት ተገቢውን ምግብ እንዳያገኙ እያደረገ ነው። ሐይቁ ከተጋረጠበት ተፈጥሯዊ አደጋ በተጨማሪ ህገ-ወጥ አስጋሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ መምጣት፣ ወደ ሐይቁ የሚገባ የደለል መጨመርና የተበከለ ቆሻሻ ወደሐይቁ መለቀቅ ሌለኛው የሐይቁ ፈተናዎች እንደሆኑ በጥናቱ መረጋገጡን ነው የገለጹት። " እነዚህ ምክንያቶች የሐይቁ የዓሣ ምርት መጠኑ እያሽቆለቆለ እንዲመጣ አድርጎታል" ብለዋል አቶ ደረጄ። "እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2011 ዓ.ም የዓሳ አምራቾቹ ቁጥር 3 ሺህ 514 ነበር፤ ዘንድሮ በተደረገ ጥናት 5 ሺህ 403 ደርሷል" ያሉት ዳይሬክተሩ እነዚህ ሁሉ ህገ-ወጥ የአሣ ማስገሪያ መረብ እንደሚጠቀሙ መታወቁን ነው የገለጹት። ዓሣ አስጋሪዎቹን ህገ-ወጥ የሚያስብላቸው የሚጠቀሙት የማስገሪያ መረብ ሳይንሳዊ ያልሆነ፣ ለመጠመድ ያልደረሱና እራሳቸውን ያልተኩ ጫጩት የአሣ ዝርያዎችን ጨምሮ የሚያጠምድ መረብ መጠቀማቸው ነው። አቶ ደረጄ እንዳሉት በሐይቁ ላይ ለማስገሪያነት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው በሌሎች አገር የተከለከለና በህገ-ወጥ መንግድ የሚገባ መረብ ነው። "ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት በአገር ውስጥ ህጋዊ መረብ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ማቋቋም አሊያም ህጋዊ መረብን ከውጪ ማስገባት ሲችል በችልተኝነት እየተመለከተው ነው" ብለዋል አቶ ደረጄ።የክልሉ እንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲም ህገ-ወጥ አስጋሪዎችን በመከታተልና በመቆጣጠር ህጋዊ ያልሆነ የማስገሪያ መረብ እንዳይጠቀሙ በማደረግ በኩል ሰፊ ክፍተት እንዳለበት ነው ያስታወቁት። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ከሰባት ዓመት በፊት አንድ የሞተር ጀልባ በአንድ ጊዜ 137 ኪሎ ግራም ዓሣ ይዞ ከሐይቁ ይወጣ ነበር በአሁኑ ወቅት ሐይቁ ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሰለባ በመሆኑ ወደ 19 ነጥብ 7 ኪሎ ግራም ዝቅ እንዲል አድርጎታል። ከአንድ ዓመት በፊት 9 ሺህ ቶን ዓሣ በዓመት የሚመረት ቢሆንም አሁን በተደረገ ጥናት ወደ 7 ሺህ ቶን ዝቅ ማለቱንም አስረድተዋል። በዓሣ ማስገር የሚተዳደሩት አቶ ባዝዘው ለገሰ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በጣና ሐይቅ ዓሣ አለ ሳይሆን ነበር ወደ ሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት “ህገ-ወጥ ማስገሪያ ስለምንጠቀም ነው” ያሉት አቶ ባዝዘው፣ ”አስጋሪዎች ይህንን ማስገሪያ ለመጠቀም ፈልገን ሳይሆን ሳይንሳዊውን ማስገሪያ የሚያቀርብልን ስለጠፋ ነው” ብለዋል። ዓሣ መተዳደሪያችን ስለሆነ ዓሣ ማስገራችን አናቆሙም" ያሉት አቶ ባዝዘው፣ ሳይንሱ የሚያዝዘውን ማስገሪያ መረብ በማቅረብ በኩል ያለው ክፍተት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል። የዓሣን ምርትን የሚረከቡት ነጋዴ ገነቱ ወንዴ በበኩላቸው ማንኛውም ሰው በፈለገው መረብ ቢያሰግር ጠያቂ እንደሌለው ገልጸዋል። "ይህም 'ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ' በሚል አመለካከት የጣናን የዓሳ ሃብት ልማት አደጋ ላይ ጥሎታል" ብለዋል። መንግስት በተለይ በህገ-ወጥ አስጋሪዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እልባት ካላበጀ በአጪር ጊዜ ውስጥ ጣና ዓሣ የሌለው ሐይቅ እንደሚሆን ተናግረዋል። ከሁለት ዓመት በፊት በቀን ከ700 እስከ 800 መቶ ኪሎ ግራም ዓሣ ከአስጋሪዎች ሲረከቡ እንደነበር ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት እየተረከቡ ያሉት ከ70 አስከ 150 ኪሎ ግራም አሳ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። የአማራ ክልል እንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የዓሳ ባለሙያ አቶ ቻላቸው አራጋው ህገ-ወጥ የዓሳ ማስገሪያ መረብ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ኤጀንሲው ጠንቅወቆ እንደሚያውቅ ተናግረዋል። "ችግሩን በቀላሉ ማስተካከል አይቻልም" ያሉት አቶ ቻላቸው እንደ እንቦጭ አረም ሁሉ አገራዊ ንቅናቄን የሚጠየቅ በመሆኑ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። እንደአቶ ቻላቸው ገለጻ እስካሁን በአገሪቱ የዓሣ ማስገሪያ ፋብሪካ ባለመኖሩ አስጋሪዎች የሚጠቀሙት ከውጪ በሚገቡ ህገወጥ መረቦች ነው። ህገ-ወጥ አሣ ማስገሪያ ወደአገር ውስጥ እንዳይገባ በድንበሮች ክትትልና ቁጥጥር የተደረገ ቢሆንም ለዘላቂ መፍትሄው ከፌዴራል ግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንደሚሰራ አስረድተዋል። በጣና ሐይቅ 28 የተለያዩ የዓሣ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን 20 ዎቹ በጣና ሐይቅ ብቻ እንደሚገኙ ከምርምሩ የተገኘ መረጃ ያስረዳል ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም