በመዲናዋ ተቆጣጣሪ ያጡት ማስታወቂያዎች የሚያደርሱት ጉዳት እየሰፋ ነው

2188

ህዳር 1/2011 በመዲናዋ የሚለጠፉና የሚሰቀሉ የውጭ ማስታወቂያዎች በህብረተሰቡና በከተማዋ ገጽታ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን ኢዜአ ያናገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ምሁራን ተናገሩ፡፡

ማስታወቂያ በሥርዓት ካልተመራ የሕብረተሰቡን መብትና ጥቅም እንዲሁም የአገርን ገጽታ ሊጎዳል የሚችል በመሆኑ ግዴታና መብትን ባማከል መልኩ የማስታወቂያ አዋጅ  759/2004   ፀድቆ ሥራ ላይ እንዲው ተደርጓል፡፡

በአዋጁ ላይ “ማንኛውም ሰው አግባብ ካለው የመንግስት አካል ፈቃድ ሳያገኝና በሕንጻ፣ በአጥር፣ በአውቶብስ ፌርማታ፣ በኤሌክትሪክ ምሰሶ፣ በቴሌኮም አገልግሎት መስጫ መሣሪያ፣ በባቡር ሀዲድ  ላይ  መለጠፍም ሆነ  መስቀል እንደማይቻል” ተደንግጓል።

በተጨማሪም ማንኛውም የውጭ ማስታወቂያ ከመንገድ  ጠቋሚ ምልክት ጋር በሚመሳሰል፣ እይታን በሚጋርድ፣ የትራፊክ እንቅስቃሴን በሚገታ ወይም የአካባቢን ገጽታና ውበት በሚያበላሽ መልኩ መቀመጥ  እንደሌለበት  በአዋጁ  ከተከለከሉ ድርጊቶች መካከል ናቸው፡፡

የኢዜአ ሪፖርተሮች  በመገናኛ ፣በፒያሳ፣ በመስቀል አደባባይና በአስኮ ሳንሱሲ አካባቢዎች  ተዘዋውረው ባደረጉት ምልከታ በአውራ ጎዳናዎች፣ በባቡር መሰረተ ልማቶች፣ በመብራት ፖሎችና በግለሰብ አጥሮች ላይ ጭምር የወረቅት ማስታወቂዎችና ያረጁ ቢልቦርዶች በስፋ ተሰቅለው  ይገኛሉ፡፡

በዚህም በከተማዋ ያለው የውጭ ማስታወቂያ አጠቃቀም ከአዋጁ ጋር የሚቃረን መሆኑን ነው ያረጋገጡት ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ  በሰጡት አስተያየት በከተማዋ የሚለጠፉ የውጭ ማስታወቂያዎች በዘፈቀደና በባለሙያ ታግዘው የተሰሩ ባለመሆናቸው ገጽታን ከማበላሸት ባለፈ የመስቀያ ቦርዶች በሰው ላይ ጉዳት እያደረሱ ናቸው፡፡

የቃላትና የፊደል ስህተቶች በማስታወቂያዎቹ ላይ በጉልህ እየታዩ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ጌታቸው ከይዘትም ባለፈ ማስታወቂያዎቹ የቅርፅ፣ የጥራትና የመቆሚያ ቦታም  ችግር አለባቸው፡፡

’’በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ስርዓት ሊያሲዝ የሚችል አካል ለመኖሩ ጥርጣሬ  አለኝ’’ ያሉት ዶክተር ጌታቸው ማስታወቂያዎች ለህብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ የሚሰጡ እንጂ ስጋት ሊሆኑ አይገባም ይላሉ፡፡

ማስታወቂያ የሀገሪቱን ባህልና ወግ ባልለቀቀ መልኩ ሊሰራ ይገባል ያሉት ዶክተሩ መልዕክታቸውን ከማስተላለፍ ባሻገር የት ቦታ ቢሰቀሉ የከተማው ገጽታ ላይ ተጸእኖ አይፈጥሩም የሚለው መታየት  አለበት ብለዋል፡፡

የሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሊያውኩ አይገባም ያለው አስተያየት ሰጪ ወጣት ሰለሞን ታዬ አሁን የሚስተዋለው ግን በአስፋልት ዳር ሆነው ችግር ሚፈጥሩና ለአደጋ የሚያጋልጡ  መሆናቸውን ነው፡፡

ሌላው የከተማ ነዋሪ እስክንድር ያሲን በበኩሉ “በከተማዋ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ስርዓት ያልተበጀላቸው በመሆኑ በግለሰብ ጊቢ በር ላይ ትዳር ፍቅር ወይም የውሹ ማስታወቂዎችን  በመለጠፍ ሰዎችን ለግጭት ሲዳርጉ አይቻለሁ’’ ነው ያሉት፡፡

ማስታወቂያዎቹ  በታዳጊ ልጆችና ጨለማን ተገን አድርጎ የሚለጠፉ በመሆኑ  ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑንም አቶ እክንድር  ይገልጻሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ባለስልጣን የህንጻ ሹም ኢንጂነር ሰለሞን ካሳ ስለጉዳዩ ተጠይቀው የውጭ ማስታወቂያ አጠቃቀም አዋጅ ከማውጣት ባለፈ የማስፈፀሚያ መመሪያ እንደሌለው ጠቅሰው ችግሩን ለመፍታት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መመሪያው  ተግባራዊ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

የውጭ ማስታወቂዎችን ያለ ፍቃድ መጠቀም ፣የመስቀያ ቦታ፣ የይዘትንና ሌሎች የዘርፉ ችግሮች  በመመሪያው የሚፈቱ መሆናቸውንም ኢንጂነር ሰለሞን  ገልፀዋል፡፡

ምርትና አገልግሎትን ማስተዋወቅ ሀሳብን ከመግለጽና ከስብዕና ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው የገለፁት ደግሞ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና የህግ ጥናት መምህር ዶክተር ተስፋዬ አባተ ናቸው ፡፡

ይዘቱም ስነ-ምግባርና ሌሎች ህጎችን ያለመጻረር፣ ሸማቾችን ያለማሳሳት፣ የሀገር ገጽታን፣ አካባቢ ጥበቃ፣ የትራፊክ ህግን፣ የማህበረሰቡን ባህልና ወግ የማክበር ግዴታዎች  እንዳለበትም  ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከህዝባዊ ተቋማት አገልግሎት ጋር  በተጻረረ  መጠቀም እንደማይቻል ያስዱት ዶክተር ተስፋዬ ህጉን የማስፈጸም ስልጣን ለብሮድካስት ባለስልጣንና በየደረጃው ለሚገኙ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች  መሠጠቱንም  ገልጸዋል፡፡

ማንም ሰው ወይም ህጋዊ ሰውነት የተሰጠው ተቋም ሀላፊነቱን መወጣት አለመቻል በሀገሪቱ የወንጀል ህግም ሆነ በፍትሐብሄር ተጠያቂ እንደሚያደርገውም ነው ያስረዱት፡፡በከተማዋ በየቦታው የሚለጠፉና የሚሰቀሉ ህገ ወጥ ማስታወቂያን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽህፈት ቤት ተግባር መሆኑን የሚገልጹት የተቋሙ የህዝብ ግንኙት  ዳይሬክተር  አቶ ጉልላት ቱፋ ናቸው ፡፡

የወረቀት ማስታወቂያዎች በግንቦች ላይ እና በመሰረት ልማቶች ላይ ፍቃድ ሳይኖራቸው ባነር የሚሰቅሉትን በህብተሰቡ ጥቆማ  እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመው ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በህገወጥ መንገድ የሚለጥፉ አካላትን አድራሻ አለማግኘት እንቅፋት እደሆነባቸው ነው የገለጹት፡፡

ዳይሬክተሩ ይሄንን ይበሉ እንጂ የህገወጥ ማስታወቂያ በከተማዋ ገጽታና በህበረተሰቡ ላይ እያስከተለ ያለው ተጽእኖ ተቆጣጣሪና ህግ የሚያስከብር አካል እንደሌለው ማሳያ መሆኑን  የኢዜአ ሪፖርተሮች ተዘዋውረው የታዘቧቸውና ያነጋገሯቸው ነዋሪዎች መረጃ ያመለክታል፡፡

የማስታወቂያ ህጉን የማስፈጸም የህግ ስልጣን ለኢትጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን  እደተሰጠ  የህግ ምሁሩ ዶክተር ተስፋዬ ቢገልጹም በየአካባቢው የሚለጠፉ ማስታወቂያና ቢልቦርድን መቆጣጠር የተቋሙ ሀላፊነት እንዳልሆነ የባለስልጣኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብረሃ   ተናግረዋል ፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በባህሪያቸው ድንበር ተሻጋሪ ከሆኑት በስተቀር በየአካባቢው የሚለጠፉና የሚሰቀሉ ማስታወቂያን ይዘት የመቆጣጠር ተግባር የተተከሉበት ከተማ አስተዳደርና ክልል  እንደሆነ ነው የጠቀሱት፡፡

በውጭ ማስታወቂያ ዘርፍ የሚሰማሩ አካላት ፈቃድ ለመውሰድ ሲመጡ ይዘቱን ከማየት ይልቅ ይዘቱን መምራት የሚያስችል እውቅትና ግብአት ማሟላታቸውን በማየት ብቻ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚሰጡም  ነው የገለጹት፡፡