የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች የማሟላት ስራ ማጠናቀቁን አስታወቀ

72
መቀሌ ህዳር 1/2011 በመቀሌ ከተማ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ መሰረተ ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች የማሟላት ስራ ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በፓርኩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ጎይተኦም ገብረኪዳን ለኢዜአ እንደገለጹት ፣የባለሃብቶች ስራና ምርት ለማቀላጠፍ የሚረዱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተከናውኗል። በፓርኩ ውስጥ ግንባታቸው ከተጠናቀቁ የመሰረተ ልማት ስራዎች መካከል  የአስር ኪሎሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ይገኝበታል። "ከመቀሌ ከተማ ወደ ኢንዳስትሪ ፓርኩ የሚወስድ ሌላው የአስር  ኪሎ ሜትር የአስፋልት  መንገድ ግንባታም በሶስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው "ብለዋል። በተጨማሪ የውሃ፣ የ24 ሰዓታት የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት እና የስልክ መስመር ዝርጋታ ስራዎች በአብዛኛው ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል። የባንክ፣የኢንቨስትመንት፣የማህበራዊ ደህንነትና የኢሚግሬሽን ማዕከላት እንዲሁም ና የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትም በተሟላ መልኩ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ ስራ አስኪያጁ እንዳመለከቱት በፓርኩ ውስጥ የእሳት አደጋ  ለመከላከልም የእሳት አደጋ መከላኪያ ብርጌድ በቋሚነት ተመድቦ እየሰራ ይገኛል። የመብራትና አገልግሎት መቆራረጥና ለሰራተኞች የሚያስፈልጉ አንዳንድ የጥቅማጥቅም የመብት ጥያቄዎች  ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።  በሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ቢሆንም አሁንም በብዛት በመሳተፍና የውጭ ቴክኖሎጂ በመቅሰም በኩል ብዙ እንደሚቀር ነው ስራአስኪያጁ ያመለከቱት። ይህንን ችግር ለመፍታት የፓርኩ ቀጣይ ትኩረት መሆኑንም ገልጸዋል። የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን ስለኤሌክትሪክ መብራት ችግር ጉዳይ ተጠይቀው" ባለሃብቶች በመብራት መቆራረጥ  ምክንያት ስራቸው እንዳይስተጓጎል የሚከታተሉ ባለሙያዎች መድበናል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በትራንስፎርሞር ችግር ምክንያት የሚያጋጥም የኃይል እጥረት ካለም ተከታትለው እንደሚያስተካክሉም ገልጸዋል። የኢንዳስትሪ ፓርኩ ስራ በመጀመሩ ተጠቃሚ መሆናቸው ከተናገሩ ሰራተኞች መካከል ወጣት መሃሪ ሙሉብርሃን  "ከስራ አጥነት ወደ ሰራተኛነት ተሸጋግሪያለሁ "ብሏል። እየሰራ የአዲስ ቴክኖሎጂ እውቀት በመገብየት ኑሮውን እየለወጠ መሆኑን  ወጣት መሃሪ ተናግሯል።  የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ 92 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በሆነ ወጪ ግንባታው ተጠናቆ ከአንድ ዓመት በፊት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መመረቁ ታውቋል፡፡                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም